በአባቻ ዘመን 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከናይጄሪያ መሸሹ ነው የሚነገረው
አሜሪካ በቀድሞው የናይጄሪያ ወታደራዊ መሪ ሳኒ አባቻ የስልጣን ዘመን የተዘረፈ 23 ሚሊዮን ዶላር ለናይጄሪያ ልትመልስ ነው፡፡
ገንዘቡን ለመመለስ የሚያስችለው ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ሳኒ አባቻ ከጎርጎሮሳውያኑ 1993 ጀምሮ ህይወቱ እስካለፈበት እስከ 1998 ድረስ በህዝብ ቁጥር እና በነዳጅ ላኪነቷ ቀዳሚ የሆነችውን ናይጄሪያን አስተዳድሯል፡፡ በዚህን ጊዜ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከናይጄሪያ መሸሹ ነው የሚነገረው፡፡ ሆኖም የተጠየቀ አልነበረም፡፡
ነገር ግን ከዚያ ወዲህ የመጡ የሃገሪቱ መንግስታት ከሃገር ወጥቶ በተለያዩ የውጭ ሃገራት እንዲከማች የተደረገውን የህዝብ ገንዘብ ለማስመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ነበረች፡፡
አሜሪካ ልመልሰው ነው ያለችው ገንዘብ በዩናይትድ ኪንግደም ባንኮች የተከማቸ ነገር ግን ዋሽንግተን እንዳይንቀሳቀስ አግዳው የነበረ እንደሆነ በናይጄሪያ የአሜሪካ አምባሳደር ሜሪ ቤት ሊኦናርድ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሯ አሜሪካ ይህን ጨምሮ ከ334 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብን ለናይጄሪያ ለመመለስ መስማማቷን ገልጸዋል፡፡
ገንዘቡ ሲመለስ የህዝብ መገልገያ ለሆኑ መሰረተ ልማቶች ልማት መዋል አለበት ስለመባሉም ነው ሲ.ኤን.ኤን የዘገበው፡፡
ናይጄሪያ ከአሁን ቀደምም በተለያዩ ጊዜያት ወጥተው በውጭ ባንኮች እንዲቀመጡ የተደረጉ ገንዘቦችን ማስመለሷ ይታወሳል፡፡
በኢህአዴግ የአገዛዝ ዘመን በህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከኢትዮጰያ እንዲወጣና በውጭ ሃገራት እንዲከማች የተደረገ ከፍተኛ ገንዘብ እንዳለ ከአሁን ቀደም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገንዘቡን ለማስመለስ ቃል በመግባት እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረው እንደነበር ይታወሳል፤ ምንም እንኳን በእርምጃዎቹ የተገኘ ውጤት ስለመኖሩ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፡፡