በአሜሪካ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ85 ሺ በላይ ሲደርስ በመላው ዓለም ከግማሽ ሚሊዮን በልጧል
በአሜሪካ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ85 ሺ በላይ ሲደርስ በመላው ዓለም ከግማሽ ሚሊዮን በልጧል
የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ይፋ ባደረገው አዲስ መረጃ አሜሪካ ከ85,500 በላይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ተገኝተውባታል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎች ቁጥር በዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ቻይና በ 81,782 እና ጣሊያን በ 80,589 ተጠቂዎች አሜሪካን ተከትለው 2ኛ እና 3ኛ ናቸው፡፡
በሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ጣሊያንን የሚስተካከላት አልተገኘም፡፡ በጣሊያን እስካሁን 8,215 ሰዎች ሲሞቱ በቻይና 3,291 በአሜሪካ ደግሞ 1,300 ህይወት አልፏል፡፡
አሜሪካ የተጠቂዎቿ ቁጥር ባልተጠበቀ መጠን ያሻቀበው፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሀገሪቱ በፍጥነት ወደ ስራ እንደምትመለስ ከተናገሩ በኋላ ነው፡፡
እስካሁን በዩኤስ 552,000 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቫይረሱ ዙሪያ ትናት ምሽት በሰጡት መግለጫ አሁንም ከቻይና ጋር የጀመሩትን የቃላት ጦርነት ቀጥለዋል፡፡ የቤጂንግ ሪፖርት ትክክለኛ ስለመሆኑ እንደሚጠራጠሩና በቻይና የሚገኙ የተጠቂዎች ቁጥር ሀገሪቱ ይፋ ካደረገችው ሊበልጥ እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ከመግለጫው በኋላ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር በስልክ በጣም ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውን በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡ ቻይና ስለቫይረሱ ለዓለም በጣም ጥሩ ግንዛቤ እንደፈጠረች እንዲሁም በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ እና ለቻይናው አቻቸው ትልቅ ክብር እንዳላቸውም በጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት በቀጣይ ቀናት እንደ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያ በአሜሪካም እየቀነሰ እንደሚመጣ ያላቸውን ተስፋ የገለጹት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሀገራቸው ተጨማሪ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ችግሩ የተንሰራፋባቸው ነገር ግን በቂ እርምጃ ያልወሰዱ ያሏቸው ሚቺጋን እና ዋሺንግተን ዲሲ ቫይረሱን ለመከላከል ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡
በአሜሪካ እስካሁን ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከስራ ገበታቸው ውጭ ሆነዋል፡፡ ይህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች በቀጣዩ ወር ከስራቸው የሚፈናቀሉ አሜሪካውያን ቁጥር ከ 40 ሚሊዮን ሊበልጥ እንደሚችል ተንብየዋል፡፡ በአሜሪካ ታሪክ ከስራቸው ተፈናቅለው የስራ አጥ ጥቅማጥቅም የጠየቁ ሰዎች ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበው በአውሮፓውያኑ 1982 ነው፡፡ በወቅቱ 695,000 ሰዎች የስራ አጥ ጥቅማጥቅም ጠይቀዋል፡፡
እስካሁን በመላው ዓለም የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 536,454 ሲደርስ ከነዚህም 24114 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ 124,395 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል፡፡
የዘገባውን መረጃዎች ከተለያዩ ምንጮች ነው ያገኘነው፡፡