አሜሪካ ዜጎቿ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ ደጋግማ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች
አሜሪካ ዜጎቿ በአፋጣኝ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።
በዩክሬን ባለው ጦርነት፣ በሩሲያ የህግ አስከባሪ ተቋማት እየተደረገ ነው በተባለ የዘፈቀደ እስራትና ወከባ አሜሪካ ዜጎቿ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ ተናግራለች።
በሞስኮ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ "በሩሲያ ውስጥ የሚኖሩ ወይም ወደ ሀገሪቱ የሚጓዙ አሜሪካዊያን ወዲያውኑ ሩሲያን መልቀቅ አለባቸው" ብሏል።
ኢምባሲው "ህጋዊ ያልሆነ የእስር አደጋ ስላለ ጥንቃቄ እንዳይለያችሁ" ሲልም አክሏል።
አሜሪካ ዜጎቿ ሩሲያን ለቀው እንዲወጡ ደጋግማ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።
እንደዚህ ያለ የመጨረሻ የህዝብ ማስጠንቀቂያ ያወጣችው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦራቸውን በከፊል ለማንቀሳቀስ ካዘዙ በኋላ በመስከረም ነበር ተብሏል።
"የሩሲያ የደህንነት አገልግሎት የአሜሪካ ዜጎችን 'በውሸት' ክስ በቁጥጥር ስር አውሏል። ሩሲያ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎችን ለእስር እና ለእንግልት እየዳረገ ነው። ፍትሃዊና ግልጽ የሆነ አያያዝ ከልክለዋል። በሚስጥር ችሎት ወይም ተአማኒነት የሌለው ማስረጃ ሳያቀርቡ ጥፋተኛ እያሉ ነው" ሲል ኤምባሲው ገልጿል።
ሩሲያ በስለላ ጠረጠርኩት ያለችውን የአሜሪካ ዜጋ የወንጀል ክስ እንደከፈተች የፌደራል ደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) በጥር ወር ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል።