የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአስቸኳይ ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ አሳሰበ
ምክር ቤቱ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ልዑክን (አትሚስ) በሚተካው ሀይል ዙርያ ምክክር አድርጓል
በውይይቱ ሶማሊያ የወደብ ስምምነቱ ካልተሰረዘ የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ ጥምር ጦር ውስጥ መካተቱን አጥብቃ ተቃውማለች
ለሶማሊያ ቀጣይ የጸጥታ ሁኔታ ወሳኝ ነው በተባለው ሳምንት በዋሽንግተን እና በኒውዮርክ የተካሄዱት ውይይቶች በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) የሚደረገው ዝግጅት በአስቸኳይ መፈጸም እንደሚኖርበት አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሸባብ ለመቆጣጠር ከዚህ ቀደም የነበረው የሰላም አስከባሪ ልዑክ በጊዜያዊነት የተካው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ልዑክ አትሚስ በመጪው ጥር ወር የሥራ ጊዜው ይጠናቀቃል።
ይህን ተከትሎም በቀጣይ ይህን የሰላም አስከባሪ ሀይል በሚተካው ልዑክ ዙርያ ባሳለፍነው ሀሙስ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ አካሄዶ ነበር።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያላንድ ጋር የተፈራረመችውን የወደብ የመግባቢያ ስምምነት እስካልሰረዘች ድረስ በአዲሰ ልኡክ ውስጥ ጦሯ እንዲሳተፍ አልፈቅድም ያለችው ሶማሊያ በአቋሟ ጸንታለች።
የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ባለፉት አስርተ አመታት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የተደረገውን ጥረት ወደ ኋላ እየመለሰው ነው ያለው ምክር ቤቱ ልዩነታቸውን በአፋጣኝ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ማሳሰቡን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል።
የሶማሊያ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሁሴን ሞአሊም “ኢትዮጵያ የወደብ ስምምነቱን የማትሰርዝ ከሆነ በአዲሱ ሰላም አስከባሪ ልዑክ ውስጥ የሚኖራትን ተሳትፎ ለራሷ ጥቅም ልትጠቀምበት ትችላለች የሚል ስጋት አለን” ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው አመት የተፈረመው አወዛጋቢው የራስ ገዟ ሶማሊላንድ እና የኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት በቀጠናው አዳዲስ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ስምምነቱ ከአንድ ክልል ጋር የተደረገ ህገ ወጥ ስምምነት ነው ያለችው ሶማሊያ ሂደቱን ልኡላዊነትን እንደመጣስ ተመልክታዋለች፡፡
በዚህም በቀጠናው በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ሲሆን ከግብጽ ጋር ያደረገችው ወታደራዊ ስምምነት ከዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ነው፡፡
ሁለቱ አካላት የሚገኙበትን ውዝግብ በድርድር ለመፍታት በቱርክ አደራዳሪነት ሁለት ጊዜ ቢገናኙም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ከትላንት በስቲያ ሀሙስ የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ በሶማሊያ አወቃቀር እና በአካባቢው በሚገኝው የጸጥታ ሁኔታ ባደረገው ምክክር አትሚስን የሚተካው ልዑክ እቅድ በቶሎ መጠናቀቅ እንደሚኖርበት አሳስቧል፡፡
በጉባኤው ላይ የተመድ ዋና ጸሀፊን ወክለው የተገኙት ጄምስ ስዋን ሁለቱም ሀገራት አለም አቀፋዊ ህግን ባከበረ መልኩ ልዩነታቸውን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተወካዩ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚገኝው ውጥረት በቀጠናው የጋራ ፍላጎታችን በሆነው ሰላም እና ደህንንት ላይ ስጋትን አስከትሏል ብለዋል፡፡
ለምክር ቤቱ ንግግር ያደረጉት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አህመድ ሞአሊም ፊቂ ኢትዮጵያ ሶማሊያ ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ትገኛለች የሚለው ሰበብ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ አባባ በአካባቢው የሚገኙ ተቃዋሚዎችን እና ታጣቂዎችን የጦር መሳርያ እያስታጠቀች ትገኛለች ሲሉ የወቀሱት ሚንስትሩ ለሰላም ማስከበሩ ሂደት ስጋት ልትሆን ትችላለች ሲሉ ፈርጀዋል፡፡
አትሚስን በሚተካው ልዑክ ላይ የኢትዮጵያ አቋም
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ካላት ቅርበት አንጻር የአል ሸባብ የሽብር ጥቃ ስጋት እንዳለባት የምትገልጽ ሲሆን ይህን ለመከላከልም በአዲሱ ልዑክ ውስጥ መሳተፍ እንደምትፈልግ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ስላሴ በአሜሪካ ኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥት ድርጅት 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ከድርጅቱ ከረዳት ዋና ፀሐፊዋ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ “የውጭ ኃይሎች ወደ ሶማሊያ የሚልኳቸው የጦር መሳሪያዎች በአሸባሪዎች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ” የሚል ስጋታቸውን መግለጻቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ከዋና ፀሐፊዋ ጋር በነበረው ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስታደርግ የነበረውን ጥረት ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ ፤ አትሚስን በሚተካው ተልዕኮ አወቃቀር ውሳኔ ላይ ከመደረሱ በፊት አስፈላጊው ውይይት መድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ማንኛው ድኅረ አትሚስን በተመለከተ የሚደረግ ሂደት መወሰን ያለበት ተልዕኮው የሚኖረውን ኃላፊነት፣ ብዛት፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና ትብብር ጨምሮ ሁሉም የተልዕኮው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በቂ ጊዜ ከተወሰደ በኋላ መሆን አንዳለበት በአጽንኦት ማንሳታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡