ብሪታንያ በዩክሬን የሚሰማሩ የአውሮፓ ወታደሮችን የመምራት አቅም እንደሌላት ተገለጸ
ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ስምምነት ከመጡ እስከ 100 ሺህ የሚደርስ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ሊሰፍሩ ይችላሉ ተብሏል

ብሪታንያ ያላት ጦር አነስተኛ መሆኑን ተከት በዩክሬን የሚሰማራውን የአውሮፓ ሰላም አስከባሪ መምራት እንደማትችል ተገልጿል
ብሪታንያ በዩክሬን የሚሰማሩ የአውሮፓ ወታደሮችን የመምራት አቅም እንደሌላት ተገለጸ፡፡
ሶስተኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ ጦርነቱ የሚቆምበት መላ እየተፈለገ ይገኛል፡፡
በተለይም የጦርነቱ ዋነኛ ደጋፊ የነበረችው አሜሪካ ለኪቭ የምትሰጠውን ድጋፍ እቀንሳለሁ ማለቷ ለዩክሬን ትልቁ ስጋት ሆኗል፡፡
በቅርቡ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬን የሚሰጡትን ገንዘብ ከመቀነሳቸው ባለፈ ከሩሲያ አቻቸው ጋር በስልክ ያወሩ ሲሆን በቅርቡም በአካል ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ሁለቱ ሀገራት የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረጉ እስከ 100 ሺህ የሚደርሱ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች በዩክሬን ሊሰፍሩ እንደሚችሉ እየተገለጸ ይገኛል፡፡
ይህን ከአውሮፓ ሀገራት የሚውጣጣ ሰላም አስከባሪ ጦር ማን ሊመራው ይችላል የሚለው ሀሳብ እየተነሳ ሲሆን ብሪታንያ አንዷ ልትሆን እንደምትችል ተገልጿል፡፡
የቀድሞ የብሪታንያ ጦር አዛዥ የነበሩት ሎርድ ዳንማት ለቢቢሲ እንዳሉት ብሪታንያ ያላት ወታደራዊ አቅም የዩክሬንን ሰላም ማስከበር ዘመቻ መምራት የሚያስችላት አይደለም ብለዋል፡፡
ተጠባበቂ ሀይሎችን ሳይጨምሮ 74 ሺህ ወታደሮች እንዳሏት የምትገለጸው ብሪታንያ የዩክሬን ሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለመምራት እስከ 44 ሺህ ወታደሮችን ማዋጣት ይጠበቅባታል ሲሉም የቀድሞው አዛዥ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን ከፈረንጆቹ 2009 እስከ 2014 የመሩት አንደርስ ጎጅ ራስሙሴን በበኩላቸው በዩክሬን ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ሰላም አስከባሪ ጦር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የዩክሬን ሰላም አስከባሪ ተልዕኮን ብሪታንያ እና ፈረንሳይ በጋራ መምራት እንደሚችሉም የቀድሞው የኔቶ ጦር መሪ አንደርስ አክለዋል፡፡