በቱርክ እና ዩክሬን ክለቦች ጨዋታ ላይ ደጋፊዎች “ፑቲን” እያሉ መዘመራቸው ዩክሬንን አስቆጣ
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን አስታውቋል
ዩክሬን የቱርኩ ክለብ ደጋፊዎች በፑቲን ስም መዘመር "አልነበረባቸውም " ብላለች
የቱርኩ እግር ኳስ ክለብ ፌነርባቼ ደጋፊዎች ከዩክሬኑ ክለብ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ የቭላድሚር ፑቲንን ስም ሲጠሩ ተደምጠው ነበር።
የፌነርባቼ ደጋፊዎች የፑቲንን ስም ጠርተው መዘመራቸው ቱርክንና ዩክሬንን ውጥረት ውስጥ ከቷል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የጀመረችው “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ቀጥሏል፡፡
ፌነርባቼ እና የዩክሬኑ ዳይናሞ ኪቭ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ እያደረጉ ነበር። በዚህ ጨዋታ ላይ የዳይናሞ ኪቩ ተጫዋች ቫይታሊቲ ቡያልስኪ አንድ ግብ አስቆጥሮ ክለቡ መምራት ይጀምራል።
በመቀጠል የቱርኩ ክለብ ፌነርባቼ ደጋፊዎች የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ስም እየጠሩ ዘምረዋል። ደጋፊዎቹ የፑቲንን ስም በማንሳት መዘመር በቱርክና በዩክሬን መካከል ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል።
የዳይናሞ ኪቭ አሰልጣኝ ድርጊቱ አሳዛኝ ነው ሲሉ የዩክሬን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ የብስጭት ጹሑፍ ጽፈዋል።
ዳይናሞ ኪቭ፤ ፌነርባቼን 2 ለ1 በማሸነፉ የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ " የዩክሬን ጦር በቱርክ መሬት ፑቲንን አሸንፈዋል፤ የፌነርባቼ ደጋፊዎችም ከአሸናፊው ጎን መሆን ነበረባቸው " ሲሉ ተናግረዋል። ከዚህ ባለፈም ዩክሬን የቱርኩ ክለብ ደጋፊዎች የፑቲንን ስም እያነሱ በመዘመራቸው ይቅርታ ልጠየቅ ይገባል እያለች ነው።
የፌነርባቼ ክለብ ፕሬዝዳንት ግን "በፍጹም ይቅርታ አንጠይቅም" ብለዋል። የክለቡ ፕሬዝዳንት የዩክሬን ባለስልጣናት አፋቸውን መሰብሰብ አለባቸው ብለዋል።
የፌነርባቼ ክለብ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች የዘመሩት መዝሙር አስፈላጊ ነው ብለው እንደማያምኑ ግን ደግሞ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
የዳይናሞ ኪቭ አሰልጣኝ በብስጭት ከጨዋታ በኋላ ሊሰጡ የነበረውን አስተያየት ሳይሰጡ ከሜዳ ወጥተዋል ተብሏል።
የፌነርባቼ ደጋፊዎች በስታዲየም ውስጥ የፑቲንን ስም እያነሱ መዘመራቸውን ተከትሎ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የማጣራት ስራ መጀመሩን አስታውቋል።