የፑቲን የክተት ጥሪን ተከትሎ በየቀኑ ወደ ጆርጂያ የሚሸሹ ሩሲያውያን ቁጥር 10 ሺህ ደርሷል ተባለ
የክሬምሊን ባለስልጣናት ፤ ሩሲያውያንን ወጣቶች እየሸሹ ነው የሚለውን ዘገባ “ሐሰት” ነው ማለታቸው አይዘነጋም
የክተት ጥሪውን ተከትሎ በአንድ ቀን ብቻ 10 ሺህ ሩሲያውያን ለመዝመት ፈቃደኛ መሆናቸውም ይታወቃል
የፑቲን የክተት ጥሪን ተከትሎ በየቀኑ ወደ ጆርጂያ የሚሸሹ ሩሲያውያን ቁጥር 10 ሺህ መድረሱ ተገለጸ።
የጆርጂያ የሀገር ውስጥ ሚኒሰትር ቫክታንግ ጎሜላውሪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “ከአራት አምስት ቀናት በፊት አስከ 6 ሺህ ሩሲያውያን በየቀኑ ወደ ጆርጂያ ይደርሱ ነበር፤ አሁን ግን በየቀኑ 10ሺህ ገደማ የሚሆኑ ሩሰያውያን ወደ ጆርጂያ እየገቡ ነው”ብለዋ።
በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ አራት ወራት ውስጥ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ሩሲያውያን ያለ ቪዛ ለአንድ አመት ሊቆዩ ወደሚችሉበት ጆርጂያ መሰደዳቸውን የሀገሪቱ ስታስቲክስ ቢሮ በሰኔ ወር ማስታወቁ አይዘነጋም።
በተመሳሳይ ጊዜ 40 ሺህ የሚያህሉ ወደ ሌላኛዋ የቪዛ እማትጠይቀው አርሜኒያ መሰደዳቸው የሚታወስ ነው።
ሚኒስቴሩ፤ ከግዳጅ እየሸሹ ያሉትን ሩሲያውያን ጆርጂያን ወደ ሚያዋስነው ድንበር ለመድረስ እንዲችሉ ወደ 5 ሺህ 500 የሚጠጉ መኪኖች የመጠባበቂያ ክምችት እንዳለ ተናግሯል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል ።
ሶሞኑን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያቀረቡትን ከፊል የክተት ጥሪን በመቃወምና ጦርነትን በመፍራት ወደ ጎረቤት ሀገራት ከሚሰደዱት በተጨማሪ በክሬምሊን ባለስልጣናት ለእስር የታዳረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሩሲያውያን እንዳሉም በርካታ መገናኛ ብዙሃን የመብት ተሟጋች ቡድን መረጃን ዋቢ በማድረግ ሲዘግቡ ተስተውለዋል።
እስካሁን በ32 ከተሞች ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረጋቸው ቢያንስ 726 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ግማሾቹ በሞስኮ ውስጥ ይገኛሉ ተብለዋል።
የሩሲያ ድርጊት ከሀገሬው ዜጎች ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድረስ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ቢሆንም፤ የክሬምሊን ባለስልጣናት ግን ድርጊቱ "ህጋዊና አግባብነት ያለው ነው" እያሉ ነው።
በተቃራኒው የክተት ጥሪውን የሚቃወሙት እንዳሉ ሁሉ፤ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያቀረቡትን የክተት ጥሪ ተከትሎ በርካታ ሩሲያውያን ፈቃደኝነታቸው እንዳሳዩም ይታወቃል፡፡
የክተት ጥሪውን ተከትሎ በአንድ ቀን ብቻ 10 ሺህ ሩሲያውያን ለመዝመት ፈቃደኛ መሆናቸውን መገለጹ አይዘነጋም።