አሜሪካ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር የመጀመሪያውን የባህር ላይ ልምምድ አደረገች
ልምምዱ የባህር ላይ ወንብድና እና ህገ-ወጥ አሳ ማጥመድን ለመከላከል ያለመ ነው ተብሏል
ምዕራብ አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዓለም የባህር ጥቃት መናኸሪያ ሆኗል ሲል የመንግስታቱ ድርጅት ገልጿል
አሜሪካና የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የመጀመሪያውን የባህር ላይ ወታደራዊ ልምምድ በጋና ቮልታ ወንዝ ላይ ማድረግ ጀምረዋል።
ልምምዱ የምዕራብ አፍሪካ ኃይሎችን ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ የልዩ ተልዕኮ ኮማንድ የአፍሪካ አዛዥ አድሚራል ሚልተን ሳንድስ የባህር ጠረፍ ያላቸው ሀገራት እንደ የባህር ላይ ወንበዴ እና ህገ-ወጥ አሳ ማጥመድ ያሉ የባህር ላይ ስጋቶችን ለመቋቋም ልምምዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ህገ-ወጥ የአሳ ማጥመድ “የሀብት መቀነስን ለመከላከል ከአጋሮቻችን ጋር ለመስራት የምንሞክርበት ጉልህ ተግባር ነው” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ህገ-ወጥ አሳ ማጥመድ ቀጣናው ቁልፍ የሆነ የምግብ ምንጭን ከመዝረፍ ባለፈ፤ አደንዛዥ እጾችን እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ጨምሮ ሌሎች የወንጀል ድርጊቶች እንዲባባስ አድርጓልም ነው ያሉት።
ከጊኒ፣ አይቮሪ ኮስት፣ ጋና እና ናይጄሪያ የተውጣጡ 350 የሚጠጉ ወታደሮች በልምምዱ መሳተፋቸው ተነግሯል።
አካባቢው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዓለም የባህር ጥቃት መናኸሪያ ሆኗል ሲል የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አስታውቋል።
በፈረንጆች 2022 መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ያወጣው ሪፖርት በህገ-ወጥ፣ እውቅና በሌለው እና ቁጥጥር ባልተደረገበት አሳ ማስገር ከምዕራብ አፍሪካ የባህር ዳርቻዎች በዓመት 9 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት እንደሚጋዝ ያመላክታል።