አሜሪካ ለዳርፉር ነጻነት እውቅና እንደማትሰጥ አስታወቀች
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች የዳርፉር ነጻነትን ለማወጅ ኤል ፋሸር የተሰኘች ከተማን ለመቆጣጠር ውጊያ ጀምረዋል ተብሏል
የሱዳን እርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት አልፎታል
አሜሪካ ለዳርፉር ነጻነት እውቅና እንደማትሰጥ አስታወቀች፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ሱዳናዊያን በጦርነቱ ምክንያት ወደ ግብጽ፣ ቻድ እና ኢትዮጵያ የተሰደዱ ሲሆን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ለሞት መዳረጋቸው ተገልጿል፡፡
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች ከሰሞኑ በዳርፉር ግዛት ካሉ ቦታዎች በብቸኝነት በሱዳን ጦር ቁጥጥርሰ ር በቆየችው ኤል ሻፈር ከተማ ለመያዝ ከባድ ውጊያ እያደረጉ ነው ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሱዳን የአሜሪካ አምባሳደር ቶም ፔሪሎ ለቢቢሲ እንዳሉት አሜሪካ በማንኛውም ሁኔታ ለዳፉር ነጻነት እውቅና አትሰጥም ብለዋል፡፡
ኤል ፋሸር በምዕራብ ዳርፉር ስር ካሉ አካባቢዎች ውስጥ በሱዳን ብሔራዊ ጦር ቁጥጥር ስር ያለች ከተማ ነች፡፡
ከተማዋ በርካታ ሱዳናዊን በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው የተጠለሉባት ከተማ ስትሆን የረድኤት ድርጅቶች መቀመጫም ነበረች፡፡
ከተጀመረ 1 ዓመት ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት፤ መፍትሄ ያልተገኘለት ቀውስ…
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች ይህችን ከተማ ከተቆጣጠረ ነጻ ዳርፉርን የመመስረት እቅድ እንዳላቸው ያስባሉ ያሉ ሲሆን ሀገራቸው ለዚህ እውቅና አትሰጥም ብለዋል፡፡
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይሎች በከተማዋ ውስጥ ባለው ሆስፒታል ላይ ባደረሳቸው ተደጋጋሚ ጥቃቶች በውጊያው የቆሰሉ ንጹሃን ህክምና እያገኙ እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡