የአሜሪካ መጠባበቂያ ነዳጅ ክምችት ከ40 ዓመት ገደማ በኋላ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ
አሜሪካ አሁን ላይ 434 ሚሊዮን በርሜል የመጠባበቂያ ነዳጅ አላት ተብሏል
የዋሸንግተን መጠባበቂያ ነዳጅ ክምችት ዝቅ ያለው በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በመናሩ ነው
የአሜሪካ መጠባበቂያ ነዳጅ ከ40 ዓመት በኋላ ቅናሽ ማሳየቱ ተገለጸ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
ጦርነቱ በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ የተለያዩ መፋለሶችን ያስከተለ ሲሆን ሀገራት ከትብብር ይልቅ ጎራ ለይተው እንዲሰለፉ እያደረገም ይገኛል።
አሜሪካ እየጨመረ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ለማረጋጋት በሚል ከመጠባበቂያ ጊዜ ነዳጅ ክምችት እያወጣች ትገኛለች።
ባለፈው ሳምንት ብቻ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከመጠባበቂያዋ በማውጣት ለዜጎቿ እንዲሸጥ አድርጋለች።
አሜሪካ ከአንድ ዓመት በፊት በመጠባበቂያ ክፍሏ ያስቀመጠችው ነዳጅ 621 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ነበር።
ይሁንና በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት መከሰትን ተከትሎ ባጋጠመ የነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በሚል ከመጠባበቂያ ክፍሏ እያወጣች በመሸጥ ላይ እንደምትገኝ ብሉምበርግ ዘግቧል።
አሁን ላይ የአሜሪካ መጠባበቂያ ነዳጅ ክምችት መጠን 434 ሚሊዮን በርሜል ላይ ደርሷልም ተብሏል።
ከፈረንጆቹ 1984 ዓመት ጀምሮ የአሜሪካ መጠባበቂያ ነዳጅ ክምችት መጠን አሁን ካለበት መጠን ዝቅ ብሎ እንደማያውቅ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
የአሜሪካ የነዳጅ አጠቃቀም መጠን በዚሁ ከቁጠለ ብሄራዊ የነዳጅ አጠቃቀም መጠን ወደ 358 ሚሊዮን በርሜል ዝቅ ይላል ተብሏል።
የዓለም ቀዳሚ ሰባት የበለጸጉ ሀገራት ስብስብ የሆነው የቡድን ሰባት ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን ማውጣታቸው ይታወሳል።
ሩሲያ በበኩሏ ነዳጇን በሚያዋጣት ዋጋ ብቻ እንደምትሸጥ ገልጻ ወደ አውሮፓ የምትልከውን ነዳጅ ሙሉ ለሙሉ ማቋረጧ አይዘነጋም።