የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪዋ ተጨማሪ የሰብዓዊ አገልግሎት መስመር ይከፈት የሚል ጥያቄ አላነሱም- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል
ዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪዋ ሳማንታ ፓወር ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል
እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ካስፈለገ ሕወሓት ከጸባ ጫሪ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ጫና ሊደረግበት እንደሚገባ መንግስት በውይይቱ ላይ አሳስቧል
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስ ኤይድ) ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ጋር በተደረገው ውይይት ተጨማሪ የሰብዓዊ አገልግሎት መስመር እንዲከፈት የሚል ጥያቄ እንዳልተነሳ የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ምሽት ላይ ከከዩኤስኤአይዲ አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር ጋር ከተወያዩ በኋላ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
መንግስት የሰብዓዊ አገልግሎት በትግራይ ክልል ተደራሽ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ እና በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለመረዳት ፓወር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡
እርዳታ በአግባቡ እንዲደርስ ካስፈለገ ሕወሓት ከጸባ ጫሪ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ጫና ሊደረግበት እንደሚገባ መንግስት በውይይቱ ላይ ማሳሰቡን ወ/ሮ ሙፈሪያት ገልጸዋል፡፡
ከመንግስት የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ በኋላ ሕወሓት በከፈተው ጥቃት ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ከአፋር እና ከአማራ ክልሎች ስለመፈናቀላቸውም አንስተዋል።
የሰብዓዊ አገልግሎት ድርጅቶች ከትግራይ ክልል በተጨማሪ እነዚህን ተፈናቃዮችም ሊደርሱ እንደሚገባ በውይይታቸው መነሳቱንም ጠቁመዋል፡፡
የዩኤስ ኤይድ ዋና አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓወር በኢትዮጵያ ስለነበራቸው ቆይታ እና ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ስላደረጉት መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።
በመግለጫቸውም በትግራይ ክልል የሚቀርበው የሰብዓዊ ድጋፍ አሁንም መፋጠን እንዳለበት ጠቁመው በዚህም ከመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል።