ዩኤስኤይድ ሚስጥራዊ ሰነዶች እንዲወገዱ አዘዘ
በቀድሞ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት የሚገኙ የገንዘብ እና እርዳታ ስርጭትን የሚያሳዩ ሰነዶች እንዲወገዱ ታዟል

ድርጅቱ ከሙስና ጋር በተያያዘ በትራምፕ አስተዳደር በቀረበበት ውንጀላ ስራ አቁሞ መሰንበቱ ይታወሳል
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ከፍተኛ ሀላፊዎች ሚስጥራዊ ሰነዶች በፍጥነት እንዲወገዱ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
ሀላፊዎቹ በኢሜል ለስራተኞች በላኩት መልዕክት በቀድሞ የድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤት ሬገን ህንጻ የሚገኙ ሰነዶችን እንዲያስወግዱ አዘዋል፡፡
በቅርቡ የተቋቋመውን የመንግስት አፈጻጸም የሚቆጣጠረውን ተቋም በሚመሩት ቢሊየነሩ ኢለን መስክ እና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩኤስኤይድ የግብር ከፋዮችን ገንዘብ አላግባብ በመጠቀም እና ሙስናን በማስፋፋት ተደጋጋሚ ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡
የፌደራል ወጪን ለመቀነስ በተደረገው ሰፊ ጥረት ኤጀንሲው 2000 ሰራተኞችን ከስራ ሲያሰናብት የቀሩትን በርካታ ሰራተኞች አስገዳጅ እረፍት እንዲወጡ አድርጓል፡፡
ተቋሙ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ለማስወገድ ባወጣው ትዕዛዝ የኤጄንሲው ተጠባባቂ ዋና ፀሃፊ ኤሪካ ካር በሮናልድ ሬገን ህንፃ ውስጥ ሚስጥራዊ የሆኑ የደህንነት እና የሰራተኞች ሰነዶችን ለማስወገድ ሙሉ ቀን ለሚደረገው ጥረት ቀሪ ሰራተኞች ማክሰኞ ወደ ቢሮ እንዲገቡ ማዘዛቸውን ፖለቲኮ መጽሄት የኢሜል መልዕክቱን ጠቅሶ ተዘግቧል።
ለሰራተኞች በተላከው የኢሜል መልዕክት ላይ “የቻላችሁትን ያህል ሰነዶች ቅዳዱ ፤ የመቅዳጃ ማሽኖች መስራት በሚያቆሙበት ወቅት ሚስጥራዊ ሰነዶችን ከላያቸው ላይ “ሚስጥር” የሚል ጽሁፍ ተጽፎባቸው በቦርሳዎች ውስጥ እንዲሰበስቡ” ያዛል፡፡
ፖለቲኮ መጽሄት እንዲወገዱ የታዘዙት ሰነዶች የገንዘብ እና እርዳታ ስርጭትን የሚያሳዩ እንዲሁም የሰራተኞችን መረጃ የያዙ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ አስነብቧል፡፡
ለሰነዶቹ መወገድ የተላከው ኢሜል ማብራሪያ ባይሰጥም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው መሰናበታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የድንበር እና ጉምሩክ ጥበቃ ተቋም በድርጅቱ ህንጻ ላይ ቢሮ ከመከራየቱ ጋር ሊገናኝ ይችላል ተብሏል፡፡
መመሪያው የፌዴራል ሰነድ አያያዝ ህጎችን እንደሚጥስ እና የኤጀንሲውን መልሶ ማዋቀር የሚቃወሙ የክስ ሂደቶችን ሊያደናቅፍ እንደሚችል በድርጅቱ የቀድሞ ሰራተኞች እና የህግ ተወካዮች ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡
የትራምፕ አጋር ኢለን መስክ የሰነዶች ማስወገድ ዘመቻውን “ማስረጃን ማውደም ወንጀል ነው” ሲል በኤክስ ገጹ ድርጊቱን አውግዟል፡፡
ኤጄንሲው በሚስጥራዊ ሰነዶች አያያዝ ዙሪያ በትራምፕ አስተዳደር ስር ምርመራ ከሚያደርገው አካል ጋር ግጭት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር 54 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የዩኤስኤይድ ፕሮጀክት ውሎች ውስጥ 90 በመቶውን ለመሰረዝ እቅድ ስለመያዙ ከዚህ ቀደም ተዘግቧል፡፡
በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሚደጎመው የልማት ድርጅት የዴሞክራሲ እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ እና የሰብአዊ ድጋፎችን ለማሰራጨት እንደተቋቋመ ቢነገርም፤ ባለፉት አመታት በሀገራት ውስጥ የመንግስት ግልበጣ ለማድረግ የአሜሪካ ስለላ ድርጅት ሲአይኤ ክንፍ ሆኖ ቆይቷል በሚል ይወነጀላል፡፡