የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ቪኒሺየስ ጁኒየር "ላሊጋው የዘረኞች ነው" አለ
የፊፋ ፐሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ጨምሮ ታዋቂ ተጫዋቾች ከቪኒሺየስ ጎን እንደሚሰለፉ ተናግረዋል
ብራዚላዊው ተጫዋች በቫሌንሽያ ደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት ደርሶበታል
የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ቪኒሺየስ ጁኒየር የስፔን ላሊጋ የዘረኞች መሰባሰቢያ ነው አለ።
ቪኒሺየስ ማድሪድ ከሜዳው ውጭ በቫሌንሸያ 1 ለ 0 በተረታበት ጨዋታ የዘረኝነት ስድብ ደርሶበታል።
ብራዚላዊው ተጫዋች በ97ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከመሰናበቱ በፊት ዳኛው የቫሌንሽያ ደጋፊዎች የዘረኝነት ስድብ እየተሳደቡ መሆኑን እንዲያጤኑ ቢነግራቸውም በቸልታ አልፈውታል።
የ22 አመቱ አጥቂ በኢንስታግራም ገፁ ላይ "ይህ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ አልያም ሶስተኛ ጥቃት አይደለም የላሊጋው መግለጫ ሆኗል፤ አወዳዳሪው አካልም ምንም አይመስለውም" ሲል ስሜቱን ገልጿል።
- የስፔን ፖሊስ በብራዚላዊው የእግርኳስ ኮከብ ላይ መስርቶት የነበረውን ክስ አቋረጠ
- ፈረንሳዊው ኮከብ ቲየሪ ሄንሪ በዘረኝነት ምክንያት ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም አቆማለሁ አለ
ላሊጋው ስፔንን የአለማችን ዘረኛ ሀገር አድርጎ እያሳላት እንደሚገኝም ነው የጠቆመው።
የዘረኝነት ጥቃቱ በየሳምንቱ ቢቀጥልም የሚከላከል አካል እንደሌለ በመጥቀስም "ዘረኝነትን ከመቃወምና ከመታገል የሚያስቆመኝ አካል የለም" ብሏል።
የስፔን ላሊጋ ፕሬዚዳንት ሀቪየር ቴቫስ በበኩላቸው ላሊጋው በስፖርት ሜዳ የሚታየውን ዘረኝነት ለመከላከል ባለፉት አመታት ጥረት ማድረጉን አንስተዋል።
ይሁን እንጂ የቪኒሺየስ ጁኒየርን "ላሊጋው የዘረኞች ነው" አስተያየት ተቃውመዋል፤ ከዚህ ቀደምም ከተጫዋቹ ጋር ለመነጋገር ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን በማንሳት።
"ላሊጋውን ከመውቀስህ በፊት የራስህን ባህሪ ለማረም ሞክር" የሚል ምላሽም ሰጥተዋል።
ቫሌንሽያ ባወጣው መግለጫ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ ደጋፊዎች ላይ "ከባድ ቅጣት እጥላለሁ" ብሏል።
የፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖም ከቪኒሺየስ ጎን እንደሚሰለፉና የዘረኝነት ጥቃት መፈፀሙን ከተረዱ ዳኛው ጨዋታውን ማስቆም ነበረባቸው ብለዋል።
የአለማችን ታዋቂ ተጫዋቾች እና የእግርኳስ ማህበራት በ22 አመቱ ተስፈኛ ተጫዋች ላይ የተፈፀመውን አሳዛኝ ተግባር እያወገዙት ነው።