የ21ኛው ክፍለ ዘመን ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪ - ቭላድሚር ፑቲን
የህግ ምሩቅ፣ የኬጂቢ ሰላይና የሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ቁልፍ መሪ ወደ ክሬምሊን ከዘለቁ 25 አመት ሆኗቸዋል
የ71 አመቱ ፑቲን ከጆሴፍ ስታሊን በኋላ ሩሲያን ለረጅም ጊዜ የሚያስተዳድሩ መሪ የሚያደጋቸውን ድምጽ አግኝተዋል
በያኔዋ ሌኒንግራድ በአሁኗ ሴንትፒተርስበርግ ህዳር 7 1952 የተወለዱት ቭላድሚር ፑቲን ከ21ኛው ክፍለዘመን ተጽዕኖ ፈጣሪ መሪዎች መካከል ከፊት ይቀመጣሉ።
በትውልድ መንደራቸው ህግ ተምረው በሩሲያ የስለላ ተቋም (ኬጂቢ) 15 አመት ያገለገሉት ፑቲን ከኬጂቢ ወጥተው ወደ ፖለቲካ የገቡትም በሴንትፒተርስበርግ ነው።
በፈረንጆቹ 1998 የሩስያ የደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) ዳይሬክተር ሆነው ተሹመው ወደ ሞስኮ ያቀኑት ፑቲን፥ ሶቪየት ህብረት ከፈራረሰች በኋላ የመጀመሪያው የሩሲያ ፕሬዝዳንት በነበሩት ቦሪስ የልትሲን የሩሲያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ በ1999 መሾማቸው ይታወሳል።
በ2000፣ 2004፣ 2012 እና 2018 በተካሄዱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች ያሸነፉት ፑቲን ከሰሞኑ በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም እስከ 2030 በስልጣን የሚያቆያቸውን ድምጽ አግኝተዋል።
ይህም ከጆሴፍ ስታሊን በኋላ ሩሲያን ለረጅም ጊዜ የሚያስተዳድሩ መሪ ያደርጋቸዋል።
ተቃዋሚዎቻቸው አምባገነን፤ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ከሶቪየት ህብረት በኋላ ገናናዋን ሩሲያ የፈጠሩ እያሉ የሚጠሯቸው ቭላድሚር ፑቲን የአለም ስርአት በአሜሪካ ብቻ መዘወሩ ይብቃ ብለው መነሳታቸውና ቻይናን ጨምሮ ሌሎች ሃያላንን ከጎናቸው ማሰለፋቸው በምዕራባውያኑ አልተወደደም።