መራጮች በዴሞክራሲ ተቋማት ያላቸው እምነት እየቀነሰ መምጣቱን ጥናት አመላከተ
በ19 ሀገራት የተደረገው የዳሰሳ ጥናት አብዛኞቹ መራጮች በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ምርጫዎች ነጻና ፍትሃዊ እንዳልሆኑ ያምናሉ ብሏል
ጥናቱ አሜሪካ ተአማኒ የምርጫ ሂደት እንዳላት የሚያምኑት ዜጎቿ 47 ከመቶ ብቻ መሆናቸውንም ጠቁሟል
መራጮች በዴሞክራሲ ተቋማት ያላቸው እምነት እየቀነሰ መምጣቱን ጥናት አመላከተ።
በስዊድን ስቶኮልም ተቀማጭነቱን ያደረገው አለማቀፉ የዴሞክራሲ ጥናት ተቋም (አይዲኢኤ) አሜሪካ ህንድና ብራዚልን ጨምሮ በ19 ሀገራት የዳሰሳ ጥናት አድርጓል።
ከየሀገራቱ 1 ሺህ 500 ሰዎች በዴሞክራሲ ተቋማት እና በሚካሄዱ ምርጫዎች ዙሪያ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በማድረግ ነው የዳሰሳ ጥናቱ የተሰራው።
በዳሰሳ ጥናቱ የቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ጣሊያን፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ ኮሪያና ታንዛኒያ ዜጎችም ተሳትፈዋል።
በ11 ሀገራት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የዳሰሳ ጥናቱ ተሳታፊዎች ዴሞክራሲን የሚጠራጠሩ፤ በቅርብ ጊዜ የተካሄዱ ምርጫዎችም ፍትሃዊ እና ነጻ ናቸው ብለው የማያምኑ መሆናቸውን ጥናቱ አመላክቷል።
ህንድና ታንዛኒያን ጨምሮ በስምንት ሀገራት ደግሞ “ስለፓርላማ እና ምርጫዎች የማይጨነቅ” ነገር ግን “ጠንካራ” መሪ እንዲኖራቸው የሚመርጡ ሰዎች በልጠው ተገኝተዋል ነው ያለው ጥናቱ።
በጥናቱ በተካተቱ ሀገራት አብዛኞቹ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ያላቸው መተማመን እጅግ ዝቅተኛ መሆኑንም ነው ያነሳው።
የፍትህ ስርአቱ ተአማኝነት ላይም ችግር እንዳለ የሚያነሳው የአለማቀፉ የዴሞክራሲ ጥናት ተቋም ጥናት፥ የዳኝነት ስርአቱ “ሁሌም ፍትህን ያሰፍናል” ብለው የሚያምኑት ከግማሽ በታች ሆነው ተገኝተዋል ማለቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኢራቃውያን ከአሜሪካ በተሻለ የፍትህ ስርአታቸው ተአማኝ እንደሆነ ያምናሉም ሲል አክሏል።
ዴንማርክ አብዛኞቹ ዜጎቿ የፍትህ ስርአታቸው ሁሉንም እኩል እንደሚያስተናግድ የሚተማመኑባት ብቸኛዋ ሀገር ናት ይላል የአይዲኢኤ ጥናት።
የዳሰሳ ጥናቱ በህዳር ወር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂደው አሜሪካ ተአማኒ የምርጫ ሂደት እንዳላት የሚያምኑት ዜጎቿ 47 ከመቶ ብቻ መሆናቸውንም ጠቁሟል።
“የዴሞክራሲ ተቋማት ህዝቡ ከሚጠብቅባቸው አንጻር በብዙ ወደኋላ ቀርተዋል” ያለው ተቋሙ፥ በዳሰሳ ጥናቱ የተገኘው ውጤትም ሰዎች ለዴሞክራሲ ያላቸው አረዳድ በሂደት እየተቀየረ መምጣቱን ያሳያል ብሏል።
በ1995 የተመሰረተውና 35 አባል ሀገራት ያለው ተቋሙ ዛሬ ይፋ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ለሌሎች ጥናቶች መነሻ እንደሚሆን አስታውቋል።