የጂፒኤስ ጠለፋ ምንድን ነው?፤ ለአቬሽን ችግር የሆነውስ እንዴት ነው?
የጠለፋ እና የስፑፊንግ ተግባር ብዙ አይነት በመሆኑ ምክንያት አየር መንገዶች ይህን ለማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለማግኘት ይቸገራሉ
የጂፒኤስ መስተጓጎል ከባለፈው አመት ወዲህ በመላው ዓለም መጨመሩ አውሮፕላኖች ከመሰመራቸው ለቀው አደጋ ሊያጋጥም ይችላል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል
ኢስቶኒያ በጥቁር ባህር የጂፒኤስ ናቪጌሽን መሳሪያዎቿን በመጥለፍ ሩሲያን ከሳለች።ይህ የኢስቶኒያ ክስ ለወራት እንዲህ አይነት ሙከራ እየተደረገብን ነው ሲሉ የነበሩትን አየርመንገዶችን ስጋት የሚያስተጋባ ነው።
የኢስቶኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጫ ያላቀረቡበት ይህ ክስ ፊንኤየር በጂፒኤስ መስተጓጎል ምክንያት በምስራቅ ኢስቶኒያ የሚያደርገውን በረራ ለአንድ ወር ማቆሙን ተከትሎ የመጣ ነው።
የጂፒኤስ መስተጓጎል በተለይ ከባለፈው አመት ወዲህ በመላው ዓለም መጨመሩ አውሮፕላኖች ከመሰመራቸው ለቀው አደጋ ሊያጋጥም ይችላል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።
ጂፒኤስ ጃሚንግ እና ስፑፊንግ ምንድን ነው?
ጂፒኤስ (ግሎባል ፖዚሺኒንግ ሲስተም) ማለት ከመርከብ እና አውሮፕላን እስከ መኪና ድረስ በመሬት ላይ ያሉትን ሁሉ የሚያስስ የሳተላይቶች እና አቅጣጫ ለመጠቆም የሚያስችሉ የመቀበያ መሳሪያዎች ጥምረት ነው።
ጂፒስ ከዚህ በፊት አውሮፕላኖች ለማረፍ ይጠቀሙበት የነበረውን አድካሚ የሬዲዮ ሲግናል የሚተካ በአቬሽን ዘረፍ በጣም አስፈላጊ የሆነ የአሰሳ መሳሪያ ነው።
ነገርግን ይህን የአስሳ መሳሪያ በቀላሉ እንዲዘጋ ወይም የተሳሳተ አቅጣጫ እንዲይዝ ማድረግ የሚቻል እንደሆነ ተገልጿል።
ጂፒኤስ የሚጠለፈው ሲግናል በሚያሰራጩ መሳሪያዎች፣ የራዲዮ ኮሙኒኬሽንን ሰብሮ በመግባት እና በአብዛኛው ደግሞ ከሳተላይት የበለጠ ጥንካሬ ያላቸውን ሲግናሎች ከመሬት በመልቀቅ ነው።
ስፑፋንግ ወይም መረጃ ከትክክለኛው አካል እንደመጣ ማስመሰል አንድ ሀገር የጠላትን አውሮፕላን ወይም ድሮን ስራውን እንዳያከናውን ለማድረግ የሚጠቅም ሲሆን ይህ ከጠለፋ የበለጠ አደገኛ ነው።
የንግድ አውርፕላኖች የጂፒኤስ መቀበያ ያንን የተሳሳተ ሲግናል ከተቀበለው ልክ ያልሆነ ሰአት ወይም ኮኦርዲኔት(አቅጣጫ) በማሳየት አብራሪውን እና የአየር ትራፊኩን በማወዛገብ ችግር ይፈጥራል።
የት ነው የሚከሰተው?
ኦፒኤስ ግሩፕ ባለፈው ታህሳስ ወር በኢራቅ፣ በኢራን እና በእስራኤል ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ ውስጥ እና በጥቁር ባህር የግል እና የንግድ አውሮፕላኖችን ያስተጓጎለ ስፑፊንግ መጨመሩን መግለጹ ይታወሳል።
ቴክኖሎጂው ድሮኖችን ከኢላማ ውጭ ለማድረግ ጥቅም ላይ እየዋለ ስለሆነ በጦርነት ቀጣና አቅራቢያ ያሉ ቦታዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። የባልቲክ ሀገራት በተለይ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ጉዳዩን ለአመታት ሪፖርት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ጠለፋ በባልቲክ ባህር መባባሱን የፊንኤየር አብራሪ እና የፊኒሽ የአብራሪዎች ማህበር የጥንቃቄ እና የጸጥታ ኮሚቴ ሊቀመንበረ ላውሪ ሶይኒ ገልጸዋል።
ሶይኒ እንዳሉት የጂፒኤስ ጠለፋ በአሁኑ ወቅት ከፖላንድ በባልቲክ በኩል እስከ ስዊድን እና ፊንላንድ ጠረፍ ድረስ እየተከሰተ ነው።
በአየር መንገዶች ላይ የሚፈጥረው ችግር ምንድን ነው?
አብዛኞቹ ዘመናዊ አየርመንገዶች አቅጣጫ ለመወሰን ከጂፒኤስ በተጨማሪ የተለያዩ ሴንሰሮችን እና ምንጮች ይጠቀማሉ።ይህ ማለት ጣልቃ የሚገባ ሲግናል ካለ ሊበሩ የማይችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።
ይሁን እንጂ አብራሪዎች እና የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች እንዳሉት ከሆነ አብዛኞቹ አየርመንገዶች በጂፒኤስ ይተማመናሉ። ጠለፋ ወይም ስፑፊንግ ከተከሰተ ጂፒኤሱ ሙሉ በመሉ ሊዘጋ እና በድጋሚ ለማስጀመር የማይቻለበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ጂፒኤሱን እንደገና ስራ ለማስጀመር የሚደረግ ሙከራ የመነሻ እና የማረፊያ ሰአት እንዲዘገይ ምክንያት ይሆናል።
የጠለፋ እና የስፑፊንግ ተግባር ብዙ አይነት በመሆኑ ምክንያት አየር መንገዶች ይህን ለማስወገድ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለማግኘት ይቸገራሉ።
በዚህ ምትክ የአየር መንገድ ባለስልጣናት አብራሪዎች ጠለፋ እና ስፑፊንግን እንዲለዩ የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት አቅደዋል።