ፖለቲካ
የዋግነር ቡድን በእንግሊዝ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ ሊፈረጅ ነው
በፕሪጎዥን የሚመራው ይህ ቡድን ባለፈው ወር በአውሮፕላን አደጋ ህይወቱን እስካጣበት ጊዜ ድረስ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደችው ባለው ጦርነት ጉልህ ሚና ተጫውቷል
የዋግነር ንብረቶች የአሸባሪ ድርጅት ንብረቶች ተብለው እንደሚመዘገቡ እና እንደሚወረሱ ተገልጿል
የሩሲያው ዋግነር ታጣቂ ቡድን በእንግሊዝ ሽብርተኛ ድርጅት ተብሎ ሊፈረጅ ነው።
በእንግሊዝ የቡድኑ አባል ወይም ደጋፊ መሆንን ህገወጥ የሚያደርግ ረቂቂ ህግ በዛሬው እለት በፖርላማ ይቀርባል።
በዚህ ረቂቅ ህግ እስከ 14 አመታት እስራት የሚያስቀጡ አንቀጾች እንደተካተቱበት ስካይ ኒውስ ዘግቧል።
በዚሁ ረቂቅ ህግ መሰረት የዋግነር ንብረቶች የአሸባሪ ድርጅት ንብረቶች ተብለው እንደሚመዘገቡ እና እንደሚወረሱ ተገልጿል።
በፕሪጎዥን ሲመራ የነበረው ይህ ቡድን ባለፈው ወር በአውሮፕላን አደጋ ህይወቱን እስካጣበት ጊዜ ድረስ ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደችው ባለው ጦርነት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ቡድኑ ከዩክሬን በተጨማሪ በሶሪያ፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሱዳን እና በሊቢያ እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።
እንግሊዝ ፍረጃው ለማድረግ ያሰበችው የቡድኑ ተፈጥሮአዊ ባህሪይ፣ የቡድኑ እንቅስቃሴ እንዲሁም በውጭ በሚኖሩ የእንግሊዝ ዜጎች ላይ የደቀነውን አደጋ ከግምት በማስገባት መሆኑን ገልጻለች።
ዋግነር ከወራት በፊት በሩሲያ መንግስት ላይ አመጽ ከፍቶ የነበረ ቢሆንም በቤላሩስ አደራዳሪነት አመጹ ቆሙ፣ የቡድኑ መሪም ወደ ቤላሩስ እንዲሄድ ተደርጎ ነበር።