“በ10 ተጫዋቾች እየተጫወትን ልንቀጥል አንችልም” - ሚኬል አርቴታ
መድፈኞቹ በዘንድሮው ሊግ የመጀመርያ ሽንፈታቸውን ባስተናገዱበት ጨዋታ በቀይ ካርድ ያጋጠማቸው የተጫዋች ጉድለት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል
የተጫዋቾች በተደጋጋሚ የቀይ ካርድ ሰላባ መሆን ቡድኑን ዋጋ እያስከፈለው ነው ብለዋል አሰልጣኙ
የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ባሳለፍነው ቅዳሜ ከበርንማውዝ ጋር ባደረጉት ጨዋታ የዊልያም ሳሊባን ቀይ ካርድ ተከትሎ ቡድናቸው በ10 ተጫዋቾች መቀጠል አይችልም ብለዋል።
ፈረንሳዊው የመሀል ተከላካይ በመጀመሪያው አጋማሽ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል በዚህም መድፈኞቹ 2-0 መሸነፋቸውን ተከትሎ በዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን አስተናግደዋል፡፡
ከብራይተን ጋር ባደረጉት ጨዋታ አማካዩ ዲክላን ራይስ ፣ ከማንቸስተር ሲቲ በአቻ ውጤት ሲለያይ የፊት አጥቂው ሊያንድሮ ትሮሳርድ በቀይ ካርድ ከተሰናበተ በኋላ ሳሊባ በዚህ የውድድር ዘመን ቀይ የተመለከተ ሶስተኛው የአርሰናል ተጫዋች ነው።
"ከ10 ተጫዋቾች መጫወት ሁሌም ችግር ያስከትላል" ያሉት አርቴታ በሶስቱም ቀይ ካርድ በተመለከቱባቸው ጨዋታዎች ቡድኑ ጎሎችን እንዳስተናገደ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጎዶሎ ተጫዋች መጫወት ቡድኑ አሁን ከሚገኝበት ፉክክር አንጻር ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው እንደሆነ ተናግረው በዚህ ሁኔታ ልንቀጥል አንችልምሲሉ ገልጸዋል፡፡
አሰልጣኙ አክለውም በቅዳሜው ጨዋታ ዊሊያም ሳሊባ ለተመለከተው ቀይ ካርድ ክለቡ ይግባኝ ሊጠይቅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
አርቴታ በታህሳስ 26 ቀን 2019 የአርሰናል አሰልጣኝ ከሆኑበት የመጀመሪያ ጨዋታ ጀምሮ እስካሁን መድፈኞቹ 18 ቀይ ካርዶችን አግኝተዋል፡፡
ይህ በተመሳሳይ ጊዜ ከሌሎች የሊጉ ክለቦች ጋር ሲነጻጸር በአምስት ብልጫ ያለው ነው።
ሳሊባ እሁድ አርሰናል በሜዳው ከሊቨርፑል ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የሚያመልጠው ቢሆንም ማክሰኞ በቻምፒየንስ ሊግ አርሰናል ከሻካታር ዶኔስክ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይሰለፋል፡፡
አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ “በሊጉ በተደጋጋሚ በተጫዋቾቻችን ላይ እየደረሰ የሚገኝውን ጫና እልህ የማክሰኞውን ጨዋታ ማሸነፍ ላይ እናውለዋለን” ብለዋል፡፡
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሊቨርፑል በ21 ፣ ማንስተር ሲቲ በ20 ፣ አርሰናል በ17 ነጥብ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።