“በኢየሩሳሌም ውስጥ ውጥረትን የሚያባብሱ ጥቃቶችን ሁሉ እናወግዛለን” መሐመድ ቢን ዛይድ
ሼህ መሐመድ ከዮርዳኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በአቡዳቢ ተገናኝተው ተወያይተዋል
የአል-አቅሳ መስጂድን ቅድስና የሚጥሱ ድርጊቶች ሁሉ መቆም እንዳለባቸው ሼህ መሐመድ አሳስበዋል
የአቡዳቢ ዘውዳዊ ልዑል እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን “በኢየሩሳሌም ውስጥ ውጥረትን የሚያባብሱ ጥቃቶችን ሁሉ እናወግዛለን” ብለዋል፡፡
ሼህ መሐመድ በአቡ ዳቢ የባህር ዳርቻ ቤተመንግስት የዮርዳኖሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ቢሽር አልካሳውኔህ ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው በኢየሩሳሌም ስላለው ጉዳይ ያነሱት፡፡
ሼህ መሐመድ እና ጠ/ሚ ዶክተር ቢሽር በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ፣ በተለይም በኢየሩሳሌው ባለው ወቅታዊ ቀውስ ፣ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
ሁለቱ አካላት በኢየሩሳሌም ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ እንደሚያሳስባቸው የገለጹ ሲሆን የአል-አቅሳ መስጂድን ቅድስና የሚጥሱ ድርጊቶች ሁሉ መቆም እንዳለባቸው ሼህ መሐመድ በውይይቱ ወቅት አሳስበዋል፡፡
ሼህ መሐመድ ፣ ከሰው ልጅ እሴቶች እና መርሆዎች ጋር የሚቃረኑ ሁሉንም ዓይነት ሁከቶች እና ጥላቻዎችን እንደሚያወግዙም የገለጹ ሲሆን በቅዱስ ከተማዋ ውስጥ ውጥረት እንዲቀጥል የሚያደርጉ ጥቃቶች እና ድርጊቶች መቆም እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር ቢሽር አልካሳውኔህ ከ ዮርዳኖስ ንጉስ አብደላህ ዳግማዊ ቢን አል ሁሴን የቃል መልእክት ለሼህ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አድርሰዋል፡፡ የዮርዳኖስ ንጉስ ዳግማዊ ቢን አል ሁሴን ለዩኤኢ እና ለህዝቦቿ ለኢድ አልፈጥር የእንኳን አደረሳችሁ እና ለሀገሪቱ ቀጣይ ደህንነት እና ብልጽግና መልካም ምኞታቸውን የሚገልጽ መልዕክት ልከዋል፡፡ ሼህ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንም በአጸፋው የዮርዳኖስ እና የህዝቦቿ ልማት ፣ ደህንነት እና ብልጽግና እንዲቀጥሉ ያላቸውን መልካም ምኞት እንዲሁም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ለንጉስ አብደላህ ዳግማዊ ቢን አል ሁሴን አስተላልፈዋል፡፡
በውይይቱ ላይ በርካታ የዩኤኢ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የዮርዳኖሱ ጠ/ሚኒስትር ልዑካንም ታድመዋል፡፡