ሩሲያ “እጅግ ከከረረ ሁኔታ ላይ ደርሰናል“ ስትል ከአሜሪካ ጋር ወደ ግጭት ልታመራ እንደምትችል አስጠነቀቀች
ሩሲያ ዋሽንግተን “ሞስኮ ያላት አማራጭ በማንም ላይ ጥገኛ እንደማትሆን መገንዘብ ብቻ ነው“ ብላለች
የክሬምሊን ቃል አቀባዩ ፔስኮቭ “አሜሪካ የሩሲያን የደህንነት ስጋቶች ለመፍታት ፈቃደኛ አይደለችም" ሲሉ ወቅሰዋል
ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የገባችበት ውጥረት ወደ ግጭት ሊያመራ ጫፍ ላይ መድረሱን አስታወቀች፡፡
ሞስኮው በመካከላቸው ያለው ውጥረት እጅግ እየተካረረ መምጣቱንና ምናልባትም ወደ ግጭት ሊያመራ እንደሚችል አስጠንቅቃለች፡፡
በሁለቱ ኃያላን ሃገራት መካከል ያለው ግንኙነት ምንም እንኳን ዲፕሎማሲያዊና ሌሎች ግንኙነቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ባያቋርጡትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየሻከረ መጥቷል፡፡ በተለይ ሩሲያ በዩክሬን ̒“ልዩ” ያለችውን ዘመቻ ከጀመረች በኋላ ግንኙነታቸው ከመሻከር አልፎ ወደ ውጥረት ተሸጋግሯል፡፡
ሆኖም ከዩክሬን ቀውስ በኋላም ቢሆን በራቸውን ለኮሚዩኒኬሽን ዝግ ሳያደረጉ ሲነጋገሩ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ላይ፤ የሩሲያ-አሜሪካ ግንኙነት ወደሚያሰጋ ደረጃ መሸጋገሩን የሩሲያው የዜና ወኪል አር.አይ.ኤ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ቃል አቀባዩ "ሞስኮ እና ዋሽንግተን ወደ ግጭት ሊያመሩ ከሚችሉበት ምእራፍ ላይ ደርሰዋል" ብለዋል፡፡
ፔስኮቭ “አሜሪካ የሩሲያን የደህንነት ስጋቶች ለመፍታት ፈቃደኛ አለመሆኗ በዶንባስ ልዩ ዘመቻ ለማድረግ ምክንያት ሆኗል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ ሩሲያን በዲፕሎማሲያዊ እና በፖለቲካዊ መንገድ መዋጋት ከንቱ እና ለውድቀት እንደሚዳርግ መረዳት አለባት ሲሉም ተናግረዋል ቃል አቀባዩ።
“ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ ጠቅላላ ጦርነት ከፍተዋል” - ላቭሮቭ
"ከአሜሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ ብቸኛው መንገድ የዋሽንግተን የበላይነትን መተው እና ሞስኮ በማንም ላይ ጥገኛ እንደማትሆን መገንዘብ ብቻ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡
አሜሪካ ቀደም ባለው የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅትም ቢሆን በሩሲያም ሆነ በማንኛውም ሀገር እንዲህ አይነት ከባድ እርምጃዎች አልወሰደችም ያሉት ቃል አቀባዩ ፔስኮቭ፤ አሜሪካ እና አጋሮቿ አሁን በሩሲያ ላይ የሚያዘንቧቸው ማዕቀቦች የሚጎዱት ሩሲያን ብቻ ሳይሆን መዕቀብ የሚጥሉትንም ጭምር መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ወታደራዊ ዘመቻ ተከትሎ ማዕቀብ ባዘነቡባት የአሜሪካ ባለስልጣናት ላይ ከሁለት ወራት በፊት ማዕቀበ መጣሏ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም የሩሲያ መንግስት በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከንና በሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወቃል፡፡
የቀድሞዋ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን፣ የኋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጀን ሳኪ እንዲሁም የመከላከያ ሚኒስትሩ ሊሎድ ኦስቲንም ማዕቀብ ከተጣለባቸው ባለስልጣናት መካከል ናቸው፡፡
ቀደም ሲል አሜሪካ በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ላይ ማዕቀብ መጣሏም አይዘነጋም።