ላቭሮቭ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ “ጠቅላላ ጦርነት” ከፍተዋል አሉ
ምዕራባዊያን የሩሲያ ደራሲዎችን፣ ሙዚቃ አቀናባሪዎችንና ሌሎች ባህላዊ ስራዎችን እየሰረዙ ነው
ጦርነቱ ምዕራባዊያን በመላው ዓለም በሚገኙ ሩሲያዊያን ላይ እየተካሄደ ነው ብለዋል
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ “ጠቅላላ ጦርነት” ከፍተዋል አሉ።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ሶስት ወራት አልፎታል።
በዚህ ጦርነት ምክንያት የዩክሬን ዋና ዋና የሚባሉ ከተሞችን ጨምሮ የንግድ ማሳለጫ ወደቦች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።
እንዲሁም ከ6 ሚሊየን በላይ ዩክሬናዊያን ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ሲሆን ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ምዕራባዊያን ሀገራት በመላው ዓለም በሚኖሩ ሩሲያዊያን ላይ ጠቅላላ ጦርነት መክፈታቸውን ተናግረዋል።
ጦርነቱ በሩሲያዊያን እና ባህላቸው ላይም ያነጣጠረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ከሩሲያ ጋር የተገናኘውን ነገር ሁሉ እርምጃ እየወሰዱ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምዕራባዊያን ሩሲያዊያን ደራሲዎችን፣ ሙዚቃ አቀናባሪዎችን እና ሌሎች ባህላዊ ስራዎችን ለዓለም ያበረከቱ ዜጎችን ስራ እየሰረዙ መሆኑንም አክለዋል።
በአሜሪካ አስተባባሪነትም ሩሲያን ለመቆጣጠር የሳተላይት ስራዎቻቸውን በማብዛት ላይ ሲሆኑ ጸረ ሩሲያ የሆኑ አመለካከቶች እንዲበዙ በተለያዩ የምዕራባዊያን ሀገራት ሙከራዎች እንዳሉም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።