መንግስት በታሰሩ ጋዜጠኞች ላይ ተዓማኒ ክስ ያቅርብ አለበለዚያ ይፍታቸው-ኢሰመኮ
በቅርቡ 7 የውጭ ሚዲያዎች የመንግስትን ፍቃድ አግኝተው ትግራይ ውስጥ ናቸው
ቢቢሲ በጋዜጠኛው መታሰር ያለውን ስጋት ለመንግስት ማሳወቁንና ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ በቅርቡ በትግራይ ክልል የተካሄደው “የጋዜጠኞችና የውጭ ሚዲያ ረዳቶች እስር” እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ እንደገለጸው መረጃ ማሳሳትና መፈብረክ በቀውሱ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ችግሮች ቢሆኑም ጋዜጠኞችን ማሰር “በምንም መልኩ ተገቢ እርምጃ” አይደለም ብሏል፡፡ ሰሞኑን የቢቢሲ ትግሬኛ ክፍል ባለደረባ ግርማይ ገብሩ መታሰሩን ተቋሙ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፋይናንሻል ታይምስና የኤኤፍፒ ጋዜጠኞችን በረዳትንት የሚያገለግሉ ሁለት ባለሙያዎች መታሰራቸውም ተዘግቧል፡፡
በቅርቡ 7 አለምአቀፍ ሚዲያዎች በትግራይ ክልል በመግባት ለመዘገብ የብሮድካት ባለስልጣንን ፍቃድ አግኝተው መዘገብ ጀምረዋል፡፡ፍቃድ ካገኙት ሚዲያዎች መካከል ቢቢሲ፣ሮይተርስ፣አልጀዚራ፣ኤኤፍፒ እንዲሁም ፋይናንሻል ታይምስ ይገኙበታል፡፡
ቢቢሲ በጋዜጠኛው መታሰር ያለውን ስጋት ለኢትዮጵያ መንግስት ማሳወቁንና ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል፡፡
የትግራይ ጊዜያዊ አስደዳደር አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን የተሳሳተ መረጃ በሚሰጡ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀው ነበር፡፡
መንግስት እስካሁን ታስሯል በተባለው ጋዜጠኛና በጋዜጠኞች ረዳቶች ጉዳይ ይፋዊ መልስ አልሰጠም፡፡
የፌደራል መንግስት የትግራይን ክልል የሚያስተዳድረው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን አሳውቆ ባካሄደው የ“ህግ ማስከበር ዘመቻ” ህዳር 19 የክልሉን ዋና ከተማ መቆጣጠሩንና ዘመቻው ማብቃቱን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በክልሉ እስካሁን የጸጥታው ሁኔታ አለመረጋጋቱንና የአብአዊ እርዳታ ለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል፡፡
መንግስት በበኩሉ በትግራይ የሰብአዊ እረዳታ እያቀረበ መሆኑንና የቀሩ የህወሓት አመራሮችን በማደን ላይ መሆኑን እየገለጸ ይገኛል፡፡