“በአምነስቲ የተጠናቀረው ሪፖርት በበቂ የመረጃ ግብዓቶች ያልተደገፈ ነው”- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አምነስቲ በክልሉ አስፈላጊውን የፊልድ ጉብኝት ቢያደርግና የሚመለከታቸውን የሃገሪቱን ባለስልጣናት ቢጠይቅ እንደሚበጅም ነው የገለጸው
ሚኒስቴሩ በሪፖርቱ ከተጠቀሱት ምንጮች መካከል “ቄስ” በሚል በመረጃ ምንጭነት የተጠቀሰው ግለሰብ በአሜሪካ የቦስተን ከተማ ነዋሪ መሆኑን አስታውቋል
በአክሱም ተፈጽመዋል ከተባሉ ግድያዎች ጋር በተያያዘ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበቂ የመረጃ ግብዓቶች ያልተደገፈ ሪፖርት ማጠናቀሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሪፖርቱ ሊያሳስብ የሚገባን ትልቅ ጉዳይ ቢያነሳም “የተጠናቀረበት መንገድ ውስንነቶች ያሉበት ነው” ያለው ሚኒስቴሩ “በአነስተኛ መረጃዎች ላይ ተመስርቶ” በምስራቃዊ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞች እና በከተማው ከሚገኙ ግለሰቦች በስልክ መጠናቀሩን አስታውቋል፡፡
በሪፖርቱ ከተጠቀሱ የመረጃ ምንጮች መካከል “ቄስ” በሚል በመረጃ ምንጭነት የተጠቀሰው ግለሰብ ቄስ ሳይሆን በአሜሪካ ቦስተን ከተማ የሚኖር “አጭበርባሪ ነው” ብሏል ሪፖርቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፡፡
በመሆኑም በእንዲህ ዓይነት የመረጃ ምንጮች ላይ የሚመሰረቱ ሪፖርቶች “የህወሓትን እና የአጋሮቹን የውሸት ፕሮፓጋንዳዎች ከማስተጋባት ውጪ ፍትሕን ሊያስጠብቁ” እንደማይችሉም ነው የገለጸው፡፡
ልክ እንደ ማይካድራው ሁሉ በአክሱም ተፈጽሟል የተባለውን ጥሰት እንደሚመረምርም “ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና ከፌዴራል ፖሊስ የተውጣጣ የምርመራ ቡድን በክልሉ ተሰማርቷል” ያለው ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
መንግስት ከአሁን ቀደም በምስራቃዊ ሱዳን ከሚገኙ ስደተኞች መካከል “አንዳንዶቹ የህወሓት የቀድሞ ተዋጊዎች ናቸው” ሲል ማስታወቁን ያስታወሰም ሲሆን “ስደተኞችን በማስፈራራትና ውሸትን በመንዛት” መጠመዳቸውን ጠቁሟል፡፡
በመሆኑም አምነስቲ እውነታውን ለማወቅ በክልሉ አስፈላጊውን የፊልድ ጉብኝት ቢያደርግና የሚመለከታቸውን የሃገሪቱን ባለስልጣናት ቢጠይቅ ይበጃልም ብሏል፡፡
ለዚህም መንግስት ለብሄራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት ለመተባበር ያለውን ዝግጁነት መግለጹንም አስታውሷል፡፡
አጋር አካላት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻልና ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ከሌሎች ብሔራዊ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው ሊሰሩ ቢችሉ ይጠቅማልም ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
ይህ ጥሰቶችን ተጨባጭ፣ ግልጽ፣ ገለልተኛ እና ያልተዳላ በሆነ መንገድ ለመመርመር የተሻለ መንገድ ሊሆን እንደሚችልም ገልጿል፡፡
በትግራይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በፍጥነት መሻሻሉንና ሰብዓዊ አስተባባሪዎች እና ብዙሃን መገናኛዎች ያለ ገደብ ወደ ክልሉ የሚገቡበት ሁኔታ መፈጠሩንም አስቀምጧል በመግለጫው፡፡