“የተሰጠኝ ኃላፊነት ከፓርቲዬ አቋም ጋር አይጋጭም” ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
አንጋፋው ፖለቲከኛ ከአዲሱ ሹመታቸው በፊትም በተለያዩ ኃላፊነቶች በመስራት ላይ ይገኛሉ
በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርን ማገልገል ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን ፕ/ር በየነ ገልጸዋል
“የተሰጠኝ ኃላፊነት ከፓርቲዬ አቋም ጋር አይጋጭም” ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በሽግግር መንግስቱ የትምህርት ሚኒስትር ደኤታ በመሆን ያገለገሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አሁንም በድጋሚ የመንግስት ኃላፊነት ቦታ ላይ መመደባቸው ተረጋግጧል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ከአል ዐይን አማርኛ ጥያቄ የቀረበላቸው ፖለቲከኛው “ለዚህ ኃላፊነት ስታጭና ስሾም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ በመሆኔ ከመግፋት ይልቅ ገብቼ በምችለው አቅም ለማገልገል ነው የምፈልገው ፤ ይህ ኃላፊነት ከፓርቲዬ አቋም ጋር አይጋጭም” ብለዋል፡፡
ፕ/ር በየነ አሁን ላይ የብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል ሲሆኑ ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር የተቋቋመው ኮሚቴ አባልም ናቸው፡፡ ”እኔ በተለያዩ ዘርፎች እያገለገልኩ ነው ፣ የአሁኑ ሹመትም አይመስለኝም ፣ የጥናትና የምርምር ሥራ ለመስራትና ለማገዝ የተመደብኩበት አድርጌ ነው የምቆጥረው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ብሔራዊ ፖሊሲ በጣም ወሳኝ እንደሆነ የሚገልጹት ፕ/ር በየነ እርሳቸው በሚችሉት ሁሉ ሀገራቸውንነና ህዝባቸውን ለማገልገል ዕድሉን በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አንጋፋው ፖለቲከኛ “ዕድል እንስጣችሁ ከተባለ ገብቶ መስራቱ የተሻለ ነው” ሲሉም ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ገዥው ፓርቲ ቤት ዘግቶ ሲሰራ እንደነበር ያስታወቁት የአሁኑ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዮት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከዚህ በኋላ እንደዚህ አይኘት ነገሮች መለመድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
“እኔ በጥናት አምናለሁ ፤ የኔ ሥራ ከሌሎች ጋር ሆኖ አጥንቶ ማቅረብ ነው ፤ እኔ በጥናት አምናለሁ ፤ የጥናት ሰው ነኝ ፤ ስለዚህ ኃላፊነቱ ምንም ችግር የለውም“ ያሉት ፕ/ር በየነ “እንዲያውም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ አካሄድ ስለሆነ በጸጋ ነው የምቀበለው“ ብለዋል፡፡
ከመሾማቸው በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚመለከተው ሰው ደውሎ እንደጠየቃቸው የገለጹት ፕ/ር በየነ በየትኛውም አጋጣሚ ሀገርን ማገልገል ዋነኛ ዓላማቸው እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ስለመሾማቸው ቢያውቁም ደብዳቤ ግን ገና እንዳልደረሳቸውም ተናግረዋል፡፡