“ከፊታችን ያሉብንን ሁለት ሃገራዊ ተልዕኮዎች በሚገባ በመወጣት ኢትዮጵያ ልጆች እንዳሏት ማረጋገጥ አለብን”- ብልጽግና
ከፊት ለፊታችን የሚጠብቁንን ሁለት ሃገራዊ ተልዕኮዎች በአንድነት እንወጣም ነው ብልጽግና ያለው
ሞትና መፈናቀል እንዲፈጠር ያደረጉ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፓርቲው አስታውቋል
ሞትና መፈናቀል እንዲፈጠር ያደረጉ ኃይሎች ስጋት በማይሆኑበት ደረጃ በቁጥጥር ስር የማዋል እና የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በባለፉት 2 ቀናት በስራ አስፈጻሚ ደረጃ የተሰበሰበው ብልጽግና ፓርቲ አስታወቀ፡፡
ብልጽግና ስብሰባውን አስመልክቶ ባወጣውና ለመንግስት ብዙሃን መገናኛዎች በላከው መግለጫ ዛሬም ከግራና ከቀኝ የሚቃጡ አደጋዎች አሉ ብሏል አደጋዎቹን ለመቀልበስ በአንድነት የሚቆምበት ወቅት እንደሆነ በመጠቆም፡፡
መግለጫው በተለይም የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት የማከናወን እና ሃገራዊ ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ የማጠናቀቅ ሁለት ሃገራዊ ተልዕኮዎች ከፊት ለፊታችን ይጠብቁናል ሲል የሚያትትም ሲሆን እነዚህን የሃገሪቱን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚወስኑ ተልዕኮዎች በብቃት በመወጣት ኢትዮጵያ ልጆች እንዳሏት ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ከሚጠናቀቅበት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ደርሰናልም ብሏል፤ ቀዳሚ ስራዎች ተጠናቀው ድምጽ የመስጠት ሂደት ብቻ እንደሚቀር በማስታወስ፡፡
ስራ አስፈጻሚው ምርጫውን በስኬት ማጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ይዞ ይመጣ፤ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚደረገውን ሽግግር ወደ አንድ ደረጃ ያሳድጋልም ነው ያለው፡፡
ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነቱን ጠብቆ እንዲፈጸምም ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመንግስት በኩል ተጀመሩ የህግ የበላይነትንና ሰላምን የማስከበር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያለው ስራ አስፈጻሚው የተፈናቀሉ ዜጎችን በፍጥነት ወደ ቀያቸው ለመመለስ የተለያዩ አካላትንና ህዝብን አስተባብሮ እንደሚሰራም ገልጿል፡፡
በትግራይ የጀመረውን የመልሶ ግንባታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ከአጋሮቹ ጋር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያስታወቀው፡፡
ስራ አስፈጻሚው “የእምነትና የብሔር ልዩነቶቻችንን እንደጸጋ በመቁጠር፤ የጀመርናቸውን ፕሮጄክቶች ሁሉ በተገቢው ደረጃ እና ፍጥነት በማጠናቀቅ፤ ከቃል ይልቅ ለተግባር ቅድሚያ በመስጠት፤ የመከላከያ ኃይላችንን በሙሉ አቅም በመደገፍ፤ የፖለቲካ አመራሮቻችንን በሃገራዊ ተልዕኮዎች ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ዲፕሎማቶቻችንን ሃገራችንን በብቃት መወከላቸውን በማስከበር” ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ወዳጆቿ ከጎኗ መቆማቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከግድቡ ጋር በተገናኘ በተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ብዙሃን መገናኛዎች ላይ በመሟገት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አድንቋል አመስግኗልም ስራ አስፈጻሚው በመግለጫው፡፡