የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች ለኒጀር ጁንታ የሰጡት ቀነ ገደብ ውድቅ ከተደረገ በኋላ ተገናኝተው ሊመክሩ ነው
ኢኮዋስ የመፈንቅለ መንግስት መሪዎች ስልጣን የማያስረክቡ ከሆነ ወታደራዊ ጣልቃ እንደሚገባ አስጠንቅቆ ነበር
የኒጀር ጁንታ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር አሊ ማሃማኔ ላሚን ዘይኔን ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሰየመ
የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች የኒጀር ጁንታ ከስልጣን የተወገዱትን ፕሬዝደንት ወደ ስልጣናቸው ለመመለስ ያስተላለፉት ማስጠንቀቂያ ውድቅ በመደረጉ ለውይይት ቀጠሮ ይዘዋል።
የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) የመፈንቅለ መንግስት መሪዎች ስልጣን እንዲያስረክቡ፤ ይህ ካልሆነ ግን ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሊገጥማቸው እንደሚችል ተናግሮ ነበር።
ነገር ግን የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ጄኔራል አብዱራሃማኔ ቲያኒ የአየር ክልል በመዝጋት ሀገሪቱን ለመከላከል ቃል ገብተዋል።
ህብረቱ በቀጥታ ምላሽ ባይሰጥም ውሳኔው ላይ ለመነጋገር ለሀሙስ ቀጠሮ ይዟል።
የአሜሪካ ተጠባባቂ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቪክቶሪያ ኑላንድ ሰኞ ዕለት ወደ ኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚ አቅንተዋል።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር "ግልጽ እና አስቸጋሪ" ውይይት ለማድረግ ወጥነዋል።
ሆኖም ወታደራዊ ባለስልጣናቱ ሀገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ትመለስ የሚለውን ጥሪ ውድቅ አድርገዋል።
የኒያሚ መፈንቅለ መንግስት መሪዎች ጠንከር ያለ አቋም በመያዝ፤ አስፈላጊ ከሆነም በጽናት ለመቆም እና ለመታገል ያላቸውን ውሳኔ ደጋግመው አረጋግጠዋል።
የጁንታ መንግስት ስልጣንን ለመጨበጥ ቀጣይነት ያለው የጸጥታ ችግርን እንደ ዋና ምክንያት ጠቅሷል።
ጁንታው በስልጣን ላይ የመቆየቱን ፍላጎት በሚያሳይ መልኩ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር አሊ ማሃማኔ ላሚን ዘይኔን ጠቅላይ ሚንስትር አድርጎ ሰይሟል።