ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ወራራ ከጀመረች ተጨማሪ ማእቀብ ሊከተላት እንደሚችል ምእራባውያን አስጠነቀቁ
ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን “ሩሲያ አንድ ትልቅ የዩክሬን አካል እየቆረጠች መሆኑን አስታውቃለች" ሲሉ ሩሲያን ከሷል
ሩሲያ ምእራባውን ሩሲያን ለመቅጣት የሚችሉትን ሁሉ እስኪያደርጉ ድረስ መቼም አይተኙም እናውቃለን ብላለች
ምእራባውያን ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ተገንጣይ ግዛቶች ላይ ወታደሮቿን ማሰማራቷን ተከትሎ በዩክሬን ላይ ሙሉ ጦርነት የምትከፍት ከሆነ ተጨማሪ ማእቀብ ሊከተላት እንደሚችል ዝቷል፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የምእራባውያን ዛቻ ከቁብ እንደማትቆጥረውና ማእቀብ እንደማያሰጋት ገልጻለች፡፡
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለዛቸው በሰጡት ምላሽ "አውሮፓውያን፣ አሜሪካውያን፣ እንዲሁም ብሪታንያውያን የኛ ወዳጆች ሩሲያን ለመቅጣት የሚችሉትን ሁሉ እስኪያደርጉ ድረስ መቼም አይተኙም" ሲሉ ተደምጧል፡፡
ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የምታደርገው ወታዳረዊ እንቅስቃሴ የጎረበጣቸው ምእራባውያን በሩሲያ ላይ የተናጠል እርምጃዎች እየወሰዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
በዚህም አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት፣ ብሪታኒያ፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ እና ጃፓን ባንኮችን ኢላማ ለማድረግ ማቀዳቸውን ሲያስታውቁ፤ ጀርመን በአውሮፓ በአስርተ አመታት ውስጥ ለታዩት አስከፊ የጸጥታ ቀውሶች ምክንያት የሆነውንና ከሩሲያ ጋር የሚገናኘውን ትልቅ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ማቆሟ ይፋ ያደረገችው ከቀናት በፊት ነበር፡፡
የዩክሬን የረዥም ጊዜ ኔቶን የመቀላቀል ግብና የሩሲያ ተቃውሞ፣ የሩሲያ ዲኔትስክ እና ሉሃንስክ ተገንጣይ ግዛቶች የይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም ይህንን ግብ ለማሳካት በምስራቅ ዩክሬን የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት በምእራባውያን ዘንዳ በአይነ ቁራኛ የሚታይ አደገኛ እንቅስቃሴ ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡
ሩሲያ የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ “የቀጠናውን ሰላም ለመጠበቅ” የምታደርገው መሆኑ በተደጋጋሚ ስትናገር ብትደመጥም አሜሪካ የሩሲያን ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ ላይ ናት፡፡
አሜሪካ ሩሲያ ያቀረበችው ምክንያት "የማይረባ" በማለትም ነበር ውድቅ ያደረገችው።
እንደ አሜሪካው ማክስር ኩባንያ መረጃ ከሆነ፡ ባለፉት 24 ሰአታት ውስጥ የታዩ የሳተላይት ምስሎች በርካታ አዳዲስ ወታደሮች እና መሳሪያዎች በምእራብ ሩሲያ እንዲሁም ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎች በደቡብ ቤላሩስ ድንበር በሚገኘው የዩክሬን የአየር ማረፊያ ላይ መኖራቸው የሚያመላክቱ ናቸው፡፡
በምእራባውያን እና ሩሲያ መካከል ያለው ውጥረትና የዲፕሎማሲ መሻከር እየተባበሰ መምጣቱን ተከትሎም፤ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን እና የፈረንሳዩ አቻቸወው ዣን ኢቭስ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ለመምከር የያዙት መርሃግብር መሰረዛቸው ተሰምቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ-ባይደን በትናንተናው እለት በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው “ሩሲያ አንድ ትልቅ የዩክሬን አካል እየቆረጠች መሆኑን አስታውቃለች፤ ይህ የሩስያ ወረራ መጀመሪያ ነው" ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ባይደን ሩሲያ ለወረራ እያኮበኮበች እንደሆነ ቢናገሩም በሩሲያው አቻቻቸው ቪላድሚር ፑቲን በኩል እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
የሩሲያ የዜና ወኪሎች የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭን ዋቢ በማድረግ እንዳሉት ከሆነ ፑቲን የጆ-ባይደንን ንግግር በቴሌቭዥን አልተመለከቱትም እናም ከተመለከቱት በኋላ ምላሽ የሚሰጥበት ጉዳይ ይሆናል፡፡
ፑቱን ለማንኛውም ችግር ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንደሚሹ ለዚህም ዝግጁ እንደሆኑ ነገር ግን "የሩሲያ ጥቅም እና የዜጎቻችን ደህንነት የማይደራደሩበት ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑ" በተለያዩ ጊዜያት ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጆ-ባይደን ይፋ ባደረጉት እቅድ መሰረት እንደ ኢስቶኒያን፣ ላቲቪያ እና ሊትዌኒያን የመሳሰሉ ሀገራት 800 እግረኛ ወታደሮችን እና እስከ ስምንት ኤፍ-35 ተዋጊ ጄቶች በኔቶ ምስራቃዊ ዳርቻ ወደሚገኙ ቦታዎች መላካቸውን ገልጸዋል፡፡