በትግራይ ከ1 ሚሊዬን ለሚልቁ ተጨማሪ ሰዎች ምግብ ለማቅረብ መቻሉን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ
ግጭቱ በተዛመተባቸው አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልሎች አስቸኳይ ድጋፍን ለማድረስ ከመንግስት ጋር እየሰራ እንደሆነም ነው ያስታወቀው
ሆኖም ፕሮግራሙ አሁንም ምግብ ከሚፈለጉት መካከል ግማሽ ያህሉን ለመድረስ አልቻልኩም ብሏል
በወርሃ ሰኔ እና ሃምሌ ባካሄዳቸው ሁለተኛ ዙር የምግብ ስርጭት ፕሮግራሞች በትግራይ ክልል ከ1 ሚሊዬን ለሚልቁ ተጨማሪ ሰዎች ምግብ ለማቅረ መቻሉን የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) አስታወቀ፡፡
ፕሮግራሙ በምግብ፣ በገንዘብ እና በሌሎች የሎጂስቲክ አቅርቦቶች በገጠሙት ችግሮች ምክንያት ለማድረስ ካቀደው ምግብ ውስጥ ግማሽ ያህሉን ለማድረስ አለመቻሉን አስታውቋል፡፡
WFP ከያዝነው ወርሃ ነሃሴ ጀምሮ ለ2.1 ሚሊዬን ሰዎች ምግብ ለማቅረብ አቅዷል፡፡ ለዚህም በሳምንት 6 ሺ ሜትሪክ ቶን ምግብ ማቅረብ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሆኖም ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በጸጥታና በሌሎችም ችግሮች ምክንያት ይህን ለማቅረብ አለመቻሉን ገልጿል፡፡
በነሃሴ የመጀመሪያ ሳምንት 175 ተሽከርካሪዎች በአብዓላ በኩል ትግራይ ደርሰዋል፡፡ ይህ የነፍስ አድን ምግብ ጭነው ክልሉ የደረሱ 90 ተሽከርካሪዎችን የሚጨምር ነው፡፡ ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን የጫኑ ተጨማሪ 90 ተሽከርካሪዎች በመጪዎቹ ቀናት በክልሉ እንደሚደርሱም ይጠበቃል፡፡
ሆኖም አብዛኛው የክልሉ ህዝብ አሁንም ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑን ተከትሎ ቢያንስ በየቀኑ እርዳታዎችን የጫኑ አንድ መቶ ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረስ እንዳለባቸው ፕሮግራሙ አስታውቋል፡፡
ግጭቱ ወደ አጎራባች የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች መዛመቱን ተከትሎ በአካባቢዎቹ አስቸኳይ ድጋፍን ለማድረስ ከመንግስት ጋር እየሰራ እንደሆነም ነው ያስታወቀው፡፡
መንግስት አሸባሪው የሕወሐት ኃይል በአጎራባች ክልሎቹ በፈጸመው ጥቃት ከ300,000 በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡