በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎች አቅርቦት ላይ ለውጥ ተደረገ
መንግስት ከአሁን በኋላ ከአጠቃላይ የክልሉ የቆዳ ስፋት 14% ያህሉን ብቻ እንደሚሸፍንም ነው ያስታወቀው
ለውጡ በተለያዩ የውጭ የረድዔት ተቋማት የሚደረጉ እርዳታዎችን ለማሳደግ የሚያስችል ነው ተብሏል
መንግስት ከዚህ በኋላ ከትግራይ ክልል አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ውስጥ በ14 በመቶው ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
ቀሪው 86 በመቶው የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ተቋማት እንደሚሸፈን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በመደረግ ላይ ካለው ሰብዓዊ ድጋፍ 70 በመቶ ያሉ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
ሁኔታውን በተመለከተ ኮሚሽነር ምትኩ በሰላም ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው የክልሉን ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ለመመለስ በሶስት መንገድ እየተሰራ ነው ተብሏል።
ሶስቱ መንገዶች ሰላም በተረጋገጠባቸው ቦታዎች ላይ ህዝቡን በማወያየት መመለስ፣ ሙሉ ሰላም ያልተረጋገጠባቸው ቦታዎች ላይ ደግሞ ስነልቦናዊ ችግሮችን ለማቅለል ስለሚደረዳ ወደዘመድ እንዲሄዱ መርዳት እና ሰላም ካልተረጋገጠባቸው ቦታዎች ለተፈናቀሉት ደግሞ ጊዜያዊ መጠለያን ማዘጋጀት የሚሉ ናቸው።
ይህ በመቀሌ እየተሰራ እንደሆነና በሽሬ እና በሌሎቹም አካባቢዎች እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
ሰብዓዊ አቅርቦቱ ከአሁን ቀደም በቀጥታ ሚኒስቴሩን በደብዳቤ በመጠየቅ ነበር ፍቃድ ባገኙ ተቋማት በኩል እንዲደርስ ሲደረግ የነበረው፡፡ አሁን ተጨማሪ 4 ተቋማት ፈቃድ አግኝተዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ተቋማቱ ኢ-ሜይል በመላክ ብቻ ድጋፎችን ለማቅረብ እና ሰራተኞቻቸውም ለመንቀሳቀስ ይችላሉ ተብሏል።
ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማድረግ አልተቻለም በሚል የሚቀርቡ ክሶችና ወቀሳዎች ከአሁን በኋላ ተቀባይነት የላቸውም ነው የተባለው፡፡
እርዳታዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መከፈታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ከክልሉ የቆዳ ስፋት 86 በመቶ ያህሉ በእርዳታ ሰጭዎች እንዲሸፈን ስለመወሰኑም ተገልጿል።
ኮሚሽነር ምትኩ “በረሀብ የሞተ ሰው የለም” ብለዋል፡፡ ሆኖም ዓለም አቀፍ ተቋማት “እርዳታ ለማግኘት ሲሉ ጉዳዩን እያስጮሁት” እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
“ልክ እንደ የመን እና ሶሪያ እርዳታ ለማግኘት ጉዳዩን እየተደረገ ያለ ሩጫ ነው” ሲሉም ነው ያስቀመጡት፡፡
አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው የተፈናቃይ ብዛት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን መሆኑንም ተናግረዋል 40 በመቶ ያህሉን ለመመለስ መታሰቡን በመጠቆም፡፡
አጣዬን በሚመለከት አማራ ክልል ለ50ሺ ተረጂዎች ድጋፍ እንዲደረግ ችግሩ በተፈጠረበት ወቅት ወዲያውኑ መጠየቁን ተከትሎ ድጋፉ በማግስቱ (ቅዳሜ ተጠይቆ እሁድ)እንዲደርስ መደረጉንም ተናግረዋል ኮሚሽነር ምትኩ ፡፡