የአለም ምግብ ፕሮግራም አውሮፕላን በአሰቸጋሪ የአየር ምክንያት ነው የተከሰከሰው- የትራንስፖርት ሚኒስቴር
የንበረትነቱ የአለም ምግብ ፕሮግራም የሆነ አነስተኛ አውሮፕላን በትናትናው እለት በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ተከስክሷል
አውሮፕላኑ 4 ሰዎችን ጭኖ የነበረ ሲሆን፤ በአብራሪዎችም ሆነ በተሳፋሪዎች ላይ ጉዳት አልደረሰም
የአለም ምግብ ፕሮግራም አውሮፕላን በአሰቸጋሪ የአየር ምክንያት መከስከሱን የትራነስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የንበረትነቱ የአለም ምግብ ፕሮግራም እንደሆነ የተነገረለት አነስተኛ አውሮፕላን በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን መከስከሱ ይታወሳል።
አውሮፕላኑ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ኮሞቦልቻ ወረዳ ቄሬንሳ ቀበሌ ጉራቻ ጋራ አሩ በተባለ ስፍራ መከስከሱም ተነግሯል።
በትራንስፖርት ሚኒስቴር በአውሮፕላን አደጋው ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
በሚኒስቴሩ የአደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ኮ/ል አምድዬ አያሌው፤ የአለም ምግብ ፕሮግራም ከአብሲንያ የበረራ አገልግሎት የተከራየው Cessna, ET-AMI መጠሪያ ስሙ UN-O763H የሆነ አውሮፕላን ለሥራ ጉዳይ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስቶ ጅግጅጋ በሰላም የደረሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም ግን ከቀኑ 7:13 ሰዓት ከጅግጅጋ ተነስቶ ወደ ድሬዳዋ ለሥራ ጉዳይ እየሄደ ሳለ ከ33 ደቂቃ በረራ በኋላ በ7:46 ላይ በአሰቸጋሪ የአየር ፀባይ ምክንያት በምሥራቅ ሀረርጌ በሀሮማያ ተራራማ አከባቢ ኮምቦልቻ ወረዳ መከስከሱን ገልጸዋል።
በአውሮፕላኑ ላይ አደጋ የደረሰበት ቢሆንም በአብራሪዎችም ሆነ በተሳፋሪዎች የደረሰ ምንም ጉዳት አለመኖሩንና ወደ ከሀረር ሆስፒታል ተወስደው በጥሩ ጤንነት ላይ ስለመሆናቸው አደጋ ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ኮ/ል አምድዬ አያሌው አብራርተዋል።
የአደጋ ምርመራ ቢሮ የምርመራ ቡድን ወደ ሥፍራው የተንቀሳቀሰ ሲሆን ምርመራው ቀጣይ ሥራ እንደሚሠራ ታውቋል።