ሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ወደ ቤላሩስ በይፋ ተዛወረ
ዝውውሩ የዋግነር መሪ ፕሪጎዝሂን ከቤላሩስ ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት የተፈጸመ ነው
እርምጃው የቤላሩስ ጎረቤትን ፖላንድ ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ከቷል
ባለፈው ሳምንት በሩሲያ ወታደረዊ አመጽ ጋር ተያይዞ ስሙ ሲነሳ የነበረው ዋግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ወደ ቤላሩስ በይፋ መዛወሩ ተነግሯል።
እርምጃው የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አመጹን ለማስቆም ከቡድኑ መስራች ኢቭጄኒ ፕሪጎዝሂን ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት የተፈጸመ ነው።
ሆኖም እርምጃው የቤላሩስ ጎረቤትን ፖላንድ ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ከቷል።
ፕሬዝዳንት ሉካሼንኮ በሰጡት መግለጫ የሩሲያ ዋግነር ቡድን መስራች ኢቭጄኒ ፕሪጎዝሂን አሁን በቤላሩስ ውስጥ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።
ፕሪጎዝሂን ወደ ቤላሩስ መሄድ ለማቅናት፤ ወታደሮቻቸው ደግሞ እሳቸውን መከተል ወይም የሩሲያን መደበኛ የጦር ኃይሎች እንዲቀላቀሉ ምርጫ ተሰጥቷቸዋል።
የቤላሩስ ፕሬዝዳንት "የዋግነር ኃይሎች በጦርነቱ ውስጥ ልምዳቸውን ለእኛ እንዲያካፍሉ እንፈልጋለን" ብለዋል።
የፖላንድ ፕሬዝዳንት አንድሬዚ ዱዳ በበኩላቸው "የዋግነር ኃይሎች ወደ ቤላሩስ ማዛወር ለእኛ አሉታዊ ምልክት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የፖላንድ ፕሬዝዳንት አክለውም የቡድኑ አዛዥ ወደ ቤላሩስ መድረሱን ተከትሎ "ዋግነር ወደ ቤላሩስ ከተዛወረ በኋላ በምስራቃዊው ግንባር ላይ የኔቶ ኃይሎችን ማጠናከር እንፈልጋለን" ብለዋል።