አማራና ትግራይ ክልሎች በቀድሞው ወሎ እና ጎንደር ክ/ሀገር ስር በነበሩት ራያና ወልቃይት አለመግባባት ላይ ናቸው
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የወልቃይት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ ቀይ መስመር መሆኑን አስታወቁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን ያሉት ዛሬ በጎንደር ከተማ ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።
"የወልቃይትን ጉዳይ ለድርድር የማናቀርበው ቀይ መስመራችን ነው" ያሉት የክልሉ ርዕሰ መንግስት የህዝብ አንድነት መጠናከር አለበት ብለዋል።
መንግስት በሽብርተኝነት የፈረጀው ህወሃት የትግራይ ግዛት የነበሩ ቦታዎችን ማለትም ወልቃይትትን በማንኛውም አማራጭ እንደሚያስመልስ ከሰሞኑ መዛቱ ይታወሳል።
የግንባሩ ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ህወሃት "ምዕራብ ትግራይ" በሚለውና ወልቃይት ጠገደ ተብሎ የሚጠራውን ቦታ በተመለከተ በቅርቡ የይገባኛል ጥያቄዎች በይፋ እንደሚያቀርቡ ቢገልፁም የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ግን በወልቃይት ድርድር እንደማያደርግ ገልጸዋል።
"የትግራይ መንግስት ያወጀው ዓላማና አቋም ነው፣ እያንዳንዱን ኢንች የትግራይን ግዛት በሚቻለው መንገድ ሁሉ በሰላማዊም ሆነ በሌላ አካሄድ ለማስመለስ ሁሉንም እናደርጋለን" ሲሉ አቶ ጌታቸው ገልጸው ነበር።
ዶ/ር ይልቃል በጎንደር ከተማ ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ አክለውም፤ "አንዳችን ለአንዳችን አስፈላጊ መሆናችንን በመገንዘብ ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ ግጭት የሚቀሰቅሱ አካላትን ማጋለጥ ይገባል"ም ብለዋል ።
ይህንን የሚያደርጉ አካላትን ማጋለጥና ለህግ ማቅረብ ይገባል ያሉት የክልሉ ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚህ በኋላ የጎንደርን ሰላም ለማናጋት የሚሰሩትን አምርሮ መታገል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የህግ ማስከበር ዘመቻው የአማራ ሕዝብን አንድነት ለማጠናከር ያለመ እንደሆነም ነው ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ያነሱት።
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንት ይልቃል የህግ ማስከበሩ የህዝብ አንድነትን ያለመ እንደሆነ ቢገልጹም ከመንግሥት ውጭ ያሉ አስተያየት ሰጭዎች ግን ሁኔታው ህግ ማስከበር እንዳልሆነ እየገለፁ ነው።