የኤርትራ ሰራዊት እንቅስቀሴ ስጋት የፈጠረባቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ምን እያሉ ነው?
የኤርትራ ወታደሮች በዚህ ሳምንት ከትግራይ ይወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ያመለክታሉ
ነዋሪዎቹ፤ የኤርትራ ወታደሮች ሲወጡ "ጌም ኦቨር፤ እኛ እንደዚህ ነን" በማለት እንደሚዙትባቸውም ተናግረዋል
በህዳር ወር 2015 መንግስት በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የሁለት አመቱ ደም አፋሳሽ ጦርነት ቆሟል፡፡
ከሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ውጪ የሆኑ የአጎራባች ክልሎች እና የውጭ ኃይሎች ከትግራይ ክልል መውጣት እንዳለባቸው በሰነዱ ላይ መጠቀሱም አይዘነጋም፡፡
እስካሁን የኤርትራ ስራዊት መውጣትን በተመለከተ በየትኛውም ወገን ማለትም በፌዴራል መንግስት፣በህወሓት እንዲሁም በኤርትራ በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ነገርግን የሰላም አደራዳሪው ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሰሞኑን ከፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበራቸው ዘለግ ያለ ቆይታ “የኤርትራ ሰራዊት ያለው በድንበር አከባቢ ነው” ማለታቸው አዲስ ነገር እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኦባሳንጆ ስለኤርትራ ወታደሮች ወቅታዊ የአሰፋፈር ሁኔታ የሰጡት አስተያየት ግን በህወሓት በኩል ተቃውሞ ሲገጥመው ተስተውሏል፡፡
ህወሓትን በመወከል የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ “የኤርትራ ወታደሮች እስካሁን ከትግራይ የመውጣት ፍላጎት የላቸውም” ሲሉ ኦሊሴጎን ኦባሳንጆን ለፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ የሰጡትን መረጃ ጠቅሰው በትዊተር ገጻቸው ተችተዋል።
አክለውም ኦባሳንጆ ያን አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት፣ የአፍሪካ ህብረት የጋራ የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ተቆጣጣሪ ቡድን ስራውን ይስራ በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል ቃል አቀባዩ።
የሰላም አዳራደሪው ኦባሳብጆን እና ጌታቸው ረዳን መረጃ መነሻ በማድረግ አል-ዐይን አማርኛ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ያናገረ ሲሆን የኤርትራ ሰራዊት ከተለያዩ ቦታዎች መንቀሳቀስ የጀመረው ገና በትናትናናው እለት ጥር 11 ቀን 2015 ዓ.ም መሆኑ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአክሱም ከተማ ነዋሪ የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ 700 ገደማ ያህሉ ተሸከርካሪዎች ከአድዋ አቅጣጫ በመምጣት በአክሱም በኩል ወደ ሽሬ ሲያልፉ ማየታቸው ተነግሯል።
በቅርቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች ከነ ወታደራዊ ሎጂስቲካቸው ወደ አድዋ አቅጣጫ አልፈው እንደነበር ያስታወሱት ነዋሪው፤ የአሁኑ እንቅስቀሴ ያልጠበቁት መሆኑም ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ማእከላዊ ዞን ከተማ የሆነችው አክሱም በፌደራል ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከሚገኙት የትግራይ ከተሞች አንዷ ናት።
ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ስር ስትሆን ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት በኋላ በከተማዋ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አይፈቀድም።
ነዋሪው እንደሚሉት ከሆነ የፌዴራል ኃይል ከገባ በኋላ በኤርትራ ወታደሮች ይደርስ የነበረው ግፍና ዘረፋ ቆሟል፡፡
ሌላው ደስታ በሚል ስም መጠራት የመረጡት የሽሬ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው የኤርትራ ወታደሮች ከተማዋን ለቀው ቢወጡም፤ አሁንም በአከባቢው እንደሚገኙና አልፎ አልፎም ለገበያ ወደ ከተማዋ እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡
“ከእሮብ እለት ሁለት ፓትሮል የያዙ የኤርትራ ወታደሮች ወታደረዊ ልብሳቸውን ለብሰው አስቤዛ ለመግዛት ወደ ከተማዋ (ሽሬ) መጥተው ነበር” ም ነው ያሉት አቶ ደስታ፡፡ ወታደሮቹ ከከታማዋ ቅርብ ርቀት ከዓዲ ጎሹ ቀጥለው ባሉ አከባቢዎች እንደሚገኙም ጭምር በመግለጽ፡፡
ሌላው አል-ዐይን ያናገራቸው የዓድግራት ነዋሪ አቶ ብርሃነም በተመሳሳይ የኤርትራ ወታደሮች በከተማዋ ቅርብ ርቀት ይገኛሉ ብለዋል፡፡
የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ከተማዋ ዓዲግራት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ከቀናት በፊት ጥር 9 ቀን 2015 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ኃይሎች የተቀበላት ከተማ መሆኗ ይታወቃል፡፡
መካላከያ ሰራዊቱ በዋናነት ከጦርነቱ በፊት ይጠቀምበት ወደ በነበረው ወታደራዊ ካምፕ መቀመጡና በከተማዋ ዙሪያ የተለያዩ እንቅስቀሴዎች በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው የተገለጸው፡፡
ቀደም ብሎ ከነበረው ሁኔታ ጋር በተያያዘ በህዝቡና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር ያለው ትምምን ምን ይመስላል በሚል አል-ዐይን አማርኛ የጠየቃቸው አቶ ብርሃነ “ጥርጣሬዎች ቢኖሩም መጥፎ የሚባል አይደለም፤ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ከተማ በሚንሳቀሱበት ወቅት ትጥቃቸው ፈተው ነው የሚንቀሳቀሱት፤ ስለዚህም ህዝቡ ምንም ስጋት የለበትም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ይሁን እንጅ የኤርትራ ሰራዊት በከተማዋ ቅርብ ርቀት ላይ መኖሩ ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሰጋ አልሸሸጉም አቶ ብርሃነ፡፡
“የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ከ20 እስከ 25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በመትገኘው ፋጺ ከተማ እንዲሁም ሶቦያ እና የዛላምበሳ ጣቢያዎች ላይ ይገኛሉ፤ ምሽግም እየቆፈሩ ነው ፤ ስለዚህም እጅጉን ስጋት አለን” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአርሶ አደር ቤቶች እየበረበሩ ወርቅ መዝረፍ እና የሰዎች እንቅስቀሴ መገደብ አሁንም ወታደሮቹ በተጠናከረ መልኩ እያከናወኑት ያለ ተግባር ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
“በኤርትራ ወታደሮች አሁንም… ስጋት አለን”
የኤርትራ ሰራዊት እንቅስቀሴ ስጋት እንዳላቸው የሽሬ፣አክሱም እና ዓድግራት ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ የኤርትራ ወታደሮች እንቅስቃሴ ሊታመን የማይችልና ከፍተኛ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ሲወጡ ለህዝቡ የሚናገሩት ዛቻ የኤርትራ መንግስት አሁንም በኢትዮጵያ ጉዳይ የቀረው ነገር እንዳለ የሚያመላክት መሆኑም ነው ነዋሪዎቹ የሚያነሱት፡፡
የኤርትራ ወታደሮች ከሚወጡበት አከባቢ ሁሉ የ”ጨዋታው አልቋል(ጌም ኦበር)፤እኛ እንዲህ ነን ! ተመልሰን እንመጣለን… ወዮላችሁ! ፣ የትም አንሄድም እዛው ምዕራብ ላይ ነን! ፣ አሸንፈናል…ወዘተ” ዛቻዎች እየተናገሩ እንደሚወጡም ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት፡፡
ስለዚህም የኤርትራ ወታደሮች ከነበለት፣ አድዋ ፣ አክሱም እንዲሁም ሽሬ መውጣት በሰሜን ምዕራብ አከባቢ ለሚገኙ ዓለም አቀፍ “እየወጣን ነው ለማለት አልያም በአከባቢው ወደ ሰፈረው ሌላው ኃይል ለመቀላቀል ያለመ ሊሆን እንደሚችልም ያላቸውን ጥርጣሬ አስቀምጠዋል” ነዋሪዎቹ፡፡
የኤርትራ ሰራዊት እንቅስቀሴን በተመለከተ አል-ዐይን አማርኛ ለህወሓት አመራሮች ቅርብ ከሆኑና ስማቸው እንዳይገለጽ ከሚፈልጉ ግለሰብ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ “እንቅስቀሴው የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ መውጣት መጀመራቸው የሚያመላክት ነው” ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጋራ የግጭት ማቆም ስምምነት አተገባበር ተቆጣጣሪ ቡድን ባስቀመጣው ቀነ ገደብ መሰረት “የኤርትራ ወታደሮች በዚህ ሳምንት ከትግራይ እንደሚወጡ”ም ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጅ የኤርትራ ወታደሮች በኤርትራ መንግስት የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሳበቸው የሰሜን ምዕራብ እንዲሁም ምስራቅ ትግራይ ዞኖች የተወሰኑ ቦታዎች ሊቆዩ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል ምንጫችን፡፡