“ጁንታው ኮማንድ ፖስቱን እና ተተኳሾቹን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አድርጓል”- ጄነራል ብርሀኑ ጁላ
ህዝብ ከኋላ እንዲመታ በህወሓት የተሰጠውን 200 መትረየስ እና ክላሽ ለሰራዊቱ ማስረከቡንም አስታውቀዋል
“ሰራዊቱ ነጥሎ ለመምታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል”ም ብለዋል ጄነራሉ
“ጁንታው ኮማንድ ፖስቱን እና ተተኳሾቹን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አድርጓል”- ጄነራል ብርሀኑ ጁላ
በህወሓት ላይ የተጀመረውን የህግ ማስከበር ወታደራዊ እርምጃ አስመልክተው ዛሬ ለብዙሃን መገናኛዎች መግለጫ የሰጡት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሀኑ ጁላ ሰራዊቱ “በሁሉም ግንባሮች ድልን እየተጎናፀፈ”እንደሚገኝ አስታወቁ።
“ጁንታው እያንዳንዳቸው 2 ሺ 500 የሰው ሀይል የያዙ 11 ብርጌድ ልዩ ሀይል፣ 14 ብርጌድ የዞን ታጣቂ እና አንድ ብርጌድ ሚሊሻ ገንብቷል” ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “አሁን ነፍስ አውጭኝ ላይ ይገኛል” ሲሉም ተናግረዋል።
ሠራዊቱ በምዕራብ ትግራይ ከዳንሻ እስከ ባዕከር ፣ አዲጎሹ ፣ አዲ ሀገራይ ፣ አዲጉዞምን ሰብሮ ትናንት ሽሬን መቆጣጠሩንም አረጋግጠዋል ።
በደቡቡ ግንባርም ከዋጃ ጀምሮ አላማጣ ፣ ኮረምን ይዞ ወደፊት ቀጥሏል።
በምስራቁ ግንባር ፣ ጨርጨር ፣ መሆኒ ፣ ራያ ቆቦና ሌሎች ቦታዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ “ጁንታውን ለህግ ለማቅረብ” በመገስገስ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።
ጄነራል ብርሃኑ “ነጻ በወጡ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ለሰራዊቱ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል”ያሉ ሲሆን “ሠራዊቱን ከኋላ እንዲመታ ቢያስታጥቁትም ምንም ሳይተኩሱ 200 መትረየስ እና ክላሽ አዲ ኮኮብ እና ሽሬ ላይ” ለሠራዊቱ እንዳስረከበ ተናግረዋል።
“ጁንታው ኮማንድ ፖስቱን እና ተተኳሾቹን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ” ማድረጉንም ነው ጄነራሉ የተናገሩት፡፡
ሆኖም “ሰራዊቱ ነጥሎ ለመምታት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል” ብለዋል ።
“ጁንታው ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት ለማስገባትና ለመበታተን ይዞት የነበረው ዕቅድ በአሁኑ ሰዓት ከሽፏል” ያሉት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ “በመከበቡ ነፍስ አውጭኝ ላይ እንደሚገኝ” ማረጋገጣቸውን መከላከያ ሰራዊቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጽ አስታወቋል፡፡