አበዳሪ ተቋማት ማግኘት የሚፈልጉት ጥቅም ምንድን ነው?
ግዙፎቹ አበዳሪዎች ብድር ከመስጠታቸው በፊት ተበዳሪ ሀገራት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደርጉ ይፈልጋሉ
አበዳሪ ተቋማት ብድር ሰጥቶ ወለድ ከመቀበል ያለፈ ፍላጎት እንዳላቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል
ግዙፎቹ አበዳሪ ተቋማት የሆኑት የአለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የአለም ባንክ ብደር ለመስጠት ተበዳሪ ሀገራት እንዲያሟሉ የሚፈልጋቸው መስፈርቶች አላቸው።
አፍሪካን የመሳሰሉ በርካታ በድህነት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት የሚኖሩባቸው የአለም ክፍሎች ኢኮኖሚያቸውን ለመደጎሚያ እና የበጀት ጉድለታቸውን ለመሙላት ከአበዳሪ ድርጅቶች እና ከሀብታም ሀገራት ብድር ይፈልጋሉ።
ብድር ፈላጊ ሀገራትም፣ ብድሩን ለማግኘት አበዳሪ ተቋማቱ የሚልጉትን የፖሊሲ ማሻሻያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ረዘም ላለ ጊዜ ከአይኤምኤፍ ጋር ድርድር አድርጋ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ፣ ብድር ማግኘት ከቻሉ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ከአይኤፍ እና ከአለም ባንክ ብድር ማግኘቱን ገልጿል።
ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ከሆነ በኋላ አይኤምኤፍ የ3.4 ቢሊዮን ዶላር መልቀቁ፣ ኢትዮጵያ ይህን እንድታደርግ ጫና ሲያደርግ እንደነበር የማያሳይ ነው።
አበዳሪ ተቋማት ብድር ሰጥቶ ወለድ ከመቀበል ባሻገር በተበዳሪ ሀገራት ውስጥ ማሳካት የሚፈልጉት ምንድን ነው? የሚለውን በተመለከት አል ዐይን አማርኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
በፈረንጆቹ 1945 የሁለተኛውን የአለም ጦርነት ማብቃት ተከትሎ በአሜሪካ የበላይ አጋፋሪነት የተመሰረቱት ሁለቱ ድርጅቶች የተቋቋሙበት የራሳቸው አላማ አላቸው፡፡
አይኤምኤፍ በጦርነቱ የተጎዳውን የአለም ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እና ለመደገፍ ሲመሰረት የአለም ባንክ በበኩሉ የመሰረተ ልማት እና ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ለሀገራት ብድር እና ድጋፍ መስጠት ጀመረ፡፡
ተቋማቱ በተመሰረቱበት አመት እየጋመ የነበረው የቀዝቃዘው የአለም ጦርነት ምድርን በሁለት ርዕዮተ አለም ከፍሎ ውጥረት ውስጥ የከተተበት ነበር ፡፡
የኮሚኒስት እና የካፒታሊስት ርዕዮተ አለሞች ከፖለቲካ ባለፈ በአለም ኢኮኖሚ አካሄድ ላይ የነበራቸውን ጽንፍ የቆመ የሀሳብ ልዩነት ከራሳቸው ተጠቃሚነት አንጻር አጋሮችን መሰበሰብ እና በተለያዩ ወታደራዊ ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ምጣኔሀብታዊ መደለያዎች ከእነርሱ ጋር የሚቆሙ ሀገሮችን የመመልመል ስራ ላይ ተጠመዱ፡፡
የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ ሽዋፈራሁ ሽታሁን የአለም ባንክ እና አይኤም ኤፍ ሚና የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው ይላሉ፡፡
“በአሜሪካ መሪነት የተቋቋሙት ሁለቱ የገንዘብ ደርጅቶች የካፒታሊዝም ሀሳብን ለማስረጽ እና የአለም ፖለቲካ ኢኮኖሚ ለእነርሱ በሚመች መንገድ ለመቅረጽ እንደ ዋነኛ መሳርያ ሆነው አገልግለዋል፡፡
የያኔው የኮሚኒስት ቀንደኛ አቀንቃኝ እና የካፒታሊስቱ አለም ተጻራሪ የነበረችው ሶቭየት ህብረት መፈራረስ የምእራባውያኑ ተጽኖ እንዲያብብ በገንዘብ እና ብደር የደሀ ሀገራትን ፖሊስ እና አስተዳደር መጠምዘዝ የሚችሉበትን ጉልበት አጎናጸፋቸው”፡፡
የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ ሲቀጥሉ “ከፍተኛ አቅም ያለው ገበያ ፣ የማአድን እና ተፈጥሮ ሀብት እንዲሁም ከፍተኛ የሰራተኛ ሀይል ያለው አፍሪካን በተለይ የምስራቅ አፍሪካን መቆጣጠር ለምእራብውያኑ ከፍተኛ ጂኦፖለቲካዊ ጥቅም ያለው ነው” ይላሉ ተንታኙ፡፡
በነጻ የሚሰጥ ብድር የለም የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ ከእያንዳንዱ ብድር እና ድጋፍ ጀርባ አንድም የኢኮኖሚ ሌላም ደግሞ ፖለቲካዊ ጥቅም ታሳቢ ተደርጎ የሚሰጥ እንደሆነ ነው የሚያነሱት፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ ባደረገቻቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መደሰታቸውን የገለጹት የአለም ባንክ እና አይኤም ኤፍ በቀጥታ ፖለቲካዊ ጥቅም ያገኛሉ ተብሎ ባይታሰብም የቻይናን እና የሩሲያን ተጽእኖ ለመቋቋም ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች መካከል በሀገራት ውስጥ የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን ማረጋገጣቸውን ማሳካት ነው፡፡
ለበርካታ የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች ኢኮኖሚዋን ክፍት ባደረገችው ኢትዮጵያ ውስጥ ኩባንያዎቻቸውን የሚያስገቡት ምዕራባውያን የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ፖሊሲ የተመቸ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡
በዚህም ብድር እና ድጋፍን እንደማስያዣ በመቁጠር የፖሊስ ለውጦችን ገቢራዊ በማድረግ ሁለት ጥቅሞችን ያገኛሉ ብለዋል ሽዋፈራሁ።
አንደኛ ኩባንያዎቻቸው ባልተነካው የደሀ ሀገራት ኢኮኖሚ ውስጥ በመሳተፍ ጥቅም የሚያገኙ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ቻይና ፣ ሩሲያ እና ወደ ሀያልነት እያደገ የመጣውን የአረቡ አለምን እንቅስቃሴ እና ተጽእኖ በቅርብ በመከታተል ጂኦፖለቲካዊ የሀይል ሚዛንን እንደሚያስጠብቁ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ይናገራሉ፡፡
በኢህዲግ ጊዜ ተመሳሳይ ፍላጎት የነበራቸው አብዳሪ ተቋማቱ የፖሊስ ለውጥ ካልተደረገ ብድር እንደማይሰጡ አቋማቸውን ሲያሳውቁ የወቅቱ መንግስት ወደ ቻይና አዘነበለ፡፡
ቻይና ብድር እና ድጋፍ ስትሰጥ እንደ ምእራባውያን የፖሊሲ ለውጦችን በቅደመ ሁኔታ ባታስቀምጥም ፣ የብድር ወለድ ምጣኔው አነስተኛ ቢሆንም በፕሮጀክት ግንባታ ላይ በነበራት ሰፊ ተሳትፎ በሰጠችው ብድር እርሷን ጠቅማለች፡፡
በአለም ባንክ እና አይኤምኤፍ አመሰራረት እና እንቅስቀሴ ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን እና ምርምሮችን ያደረጉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ሀሳብ እንዳሉት፤አሁን ላይ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች በስፋት ተግባራዊ እንዲደረግ የሚፈልገው የፖሊሲ ለውጥ አሜሪካ ፣ አይኤምኤፍ እና የአለም ባንክ በጋራ ያዘጋጁት (The Washington Consensus) የተባለው ማዋቅራዊ ማሻሻያዎች እንዲደርግ ከሚያዘው የፖሊሲ ስምምነት የሚነጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አክለውም የሀገራት የእድገት ልማት ለካፒታሊስቱ አለም በሚመች መልኩ እንዲቀረጽ የሚያዘው ይህ የሶስትዮሽ ስምምነት በተለይ በ1980ዎቹ በተለያዩ ሀገራት ላይ ኢኮኖሚያው ጉዳትን አስከትሎ እንደነበር ያነሳሉ፡፡
“ስምምነቱ ስትራክቼራል አጀስመንት (መዋቅራዊ ማሻሻያ) በሚል የተቀነበበ ሲሆን መንግስት ለኢኮኖሚው የሚደርገውን ድጎማ እንዲያነሳ ፣ ገበያውን ክፍት እንዲያደርግ ፣ የታክስ አሰባሰቡን እንዲያሻሽል እና ገቢውን እንዲጨምር ፣ በመንግስት የተያዙ የልማት ድርጅቶች በሙሉ ለግል ባለሀብት እንዲሸጡ የሚጠይቅ ነው፡፡
ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላ ቅኚ ገዢዎች በአፍሪካ ውስጥ አቋቁመዋቸው የነበሩ ግዙፍ ኩባንያዎችን የተቋቋሙ መንግስታት ወርሰዋቸው ነበር፡፡
መንግስት ገበያውን ከፍት ማድረግ አለበት በሚለው እሳቤ የልማት ድርጅቶቹ ለሽያጭ ክፍት ሲሆኑ ኩባንያዎቹን መልሰው የገዟቸው ቅኝ ገዢ ሀገራት እንደነበሩ” ዶክተር ቆስጠንጢኖስ አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ብድሮች ያለፍላጎት እና ጥቅም ይሰጣሉ ብሎ ማሰብ አዳጋች መሆኑን የሚጠቅሱት የኢኮኖሚ ባለሙያው ተወደደም ተጠላም አለም የምትመራው በካፒታሊስት አለም በመሆኑ የኢኮኖሚ ነጻነት የሌለው ሀገር ከተጽእኖ ውጭ ሊሆን እንደማይችል ነው የሚናገሩት፡፡
ቻይና እና ሩስያን የመሳሰሉ ሀገራት ከምእራቡ አለም ጋር ከፍተኛ ሽኩቻ ውስጥ የሚገኙት ይህን ተጽእኖ መቋቋም በመቻላቸው እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብድር በራሱ መጥፎ አይደለም ይላሉ “ብድር መጥፎ የሚሆነው በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ሳይውል ቀርቶ ወደ እዳነት ሲቀየር ነው፡፡ ከአለም የንግድ ስርአት ጋር ተወዳድረን እንጓዛለን ተብሎ ካተቀደ ኢኮኖሚው ክፍት መደረጉ ላይጎዳ ይችላል፡፡
ነገር ግን የምናገኛቸውን ብድሮች ወደ ምርታማነት መቀየር እና መንግስት ምርት ለማስገባትም ሆነ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማጥበብ ይኖርብናል” ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የኢኮኖሚውን መከፈት ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ኩባንያዎች ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ቢደረግ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ስለሚንቀሳቀሱ መንግስት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ማከፋፈል የሚችልበትን አቅም ያዳብረለታል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ሰፊ ርብርብ ማድረግ እና የመንግስት ወጪን መቀነስ ከአበዳሪ አከላት ጥገኝነት የሚያላቅቀን መንገድ እንደሆነ ተነስቷል፡፡
የኢኮኖሚ ፖለቲካ ተንታኙ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ብደር ማግኝት እንደስኬት የሚታየው ወጭውን ሊመልሱ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ሲውል ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋትን ከሚያስከትሉ ስራ አጥነት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የኑሮ ውድነትን ማሻሻል ላይ የሚሰራበት ከሆነ አበዳሪዎቹ የሚያስቀምጡትን ቅድመ ሁኔታ ለመቋቋም ስለሚያስችል እንደስኬት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል፡፡
ከፍላጎቱ ጋር የሚጣጣም ምርት በገበያው ውስጥ ማሰራጨት ከተቻለ የዋጋ ንረት ስለሚቀንስ በሀብታም እና በድሀ መካከል ያለው የኑሮ ልዩነት እንዲቀንስ ዜጎችም ገንዘብ ቆጥበው ሀብት ማፍራት የሚችሉበትን እድል ስለሚፈጥር ምርታማነት ላይ መስራት ወሳኝ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
ሁለቱም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ኢኮኖሚ ያለ ሰላም እንደማይታሰብ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡
ኢኮኖሚው የትኛውንም አይነት ማሻሻያ እና የቱንም አይነት የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ቢደረግለት ሰላም ካልተረጋገጠ ልማትን ማምጣት ስለማይቻል የሚደረጉ ማሻሻያዎች ተጨማሪ ቀውስን እንዳያስከትሉ ፖለቲካዊ መረጋጋትን እና ሰላምን ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡
በተጨማሪም ሀገር ከኢኮኖሚ ጥገኝት አየተላቀቀች በሄደች ቁጥር የብድር እና የሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ስለሚቀንስ ተጽኖውን መቋቋም ያስችላል ብለዋል፡፡