ህገመንግስት የሚተረጉመው የ”ህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ” ስልጣንና አወቃቀር ምን ይመስላል?
ህገመንግስት የሚተረጉመው የ”ህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ” ስልጣንና አወቃቀር ምን ይመስላል?
የዘንድሮው ምርጫ ተራዝሞ “ህገመንግስታዊ ትርጉም” አንዲሰጥ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
ይህን ትርጉም የሚሰጠው የ“ህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ” አነማንን አካቷል?፤ አደረጃጀቱ ምን ይመስላል? የሚሉ ጥያቄዎች ትኩረት እየሳቡ ይገኛሉ፡፡
ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ነሀሴ 23፣2012 ዓ.ም ሊያካሂደው ቀን ቆርጦለት የነበረው “ምርጫ 2012” አለምአቀፋዊ በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በመከሰቱ ምክንያት ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ እንደማይችል ባለፈው ወር አስታውቆ ነበር፡፡
በወቅቱ ቦርዱ መቼ ይካሄድ የሚል ቀን ባያስቀምጥም፤ ምርጫው ግን መራዘም እንዳለበት ገልጾ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ህገመንግስት መሰረት ምርጫ በየ 5 አምስት አመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ምርጫ መካሄድ ካለበት ጊዜ ሲያልፍ፣ የመንግስትም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት እድሜ ያበቃል ማለት ነው፡፡
ይህን የሚደነግገው የህገመንግስቱ አንቀጽ በ“ህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ” አንዲተረጎም በመንግስት አቅራቢነት በተወካዮች ምክርቤት ባለፈው ማክሰኞ ጸድቋል፡፡
ጉባኤው የተቋቋመበት አላማ?
የህገመንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በ1993ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ ጉባኤው በአዋጅ ቁጥር 250/1993 ተቋቁሞ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሟል፡፡
ጉባኤውን ለማጠናከር በ2005 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ቁጥር 789/2005 አንቀጽ 3 (1) እንደተደነገገው ጉባኤው “ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር ወይን የመንግስት አካል ውሳኔ ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከህገመንግስቱ ጋር ይቃረናል የሚል ጥያቄ በጽሁፍ ሲቀርብለት ያጣራል፡፡በሚያደርገው ማጣራት መሰረት ህገመንግስቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌደሬሽን ምክርቤት የውሳኔ ሀሳብ ያቀርባል፡፡”
በዚህ አዋጅ መሰረት ጉባኤው የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገ-መንግስት በተሟላ መልኩ ስራ ላይ እንዲውልና ህገ-መንግስታዊ ትርጉም የሚስፈልጋቸውን ጉዳዮች እያጣራ በህግ ስልጣን ለተሰጠው ለፌደሬሽን ምክርቤት እንዲያቀርብ ታስቦ ነው፡፡
የጉባኤው አደረጃጀት ምን ይመስላል?
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ፕሬዘዳንት--ሰብሳቢ
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ምክትል ፕሬዘዳንት--ምክትል ሰብሳቢ
በፕሬዘዳንቱ/ቷ የሚሾሙ ስድስት የህግ አማካሪዎች--አባላት
ከፌደሬሽን ምክርቤት አባለት በፌደሬሽኑ የሚመረጡ 3 ሰዎች--አባላት
ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ቢሆንም “ምርጫ 2012” ይካሄድም፣ አይካሄድ እና የሽግግር መንግስት ይቋቋም በሚሉ ፓርቲዎች መካከል ልዩነት ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሰላለፍ
መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው እንደሚካሄድ ሲገልጽ ቆይቶ ነበር፡፡ አሁን ላይ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫውን ለማካሄድ እንዳማይቻልና ህጋዊ መፍትሄ ያላቸውን አማራጮች በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል አቅርቦ ነበር፡፡
ምክርቤቱን መበተን፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፤ ህገመንግስት ማሻሻልና ህገመንግስትዊ ትርጓሜ መስጠት የሚሉ አማራጮች በባለሙያዎች አስጠናሁ ያለው መንግስት መንግስት፤ ህገመንግስታዊ ትርጉም የሚለውን ምክረ ሀሳብ መርጧል፡፡
ዋና ታቃዊሚ የሚባሉት የኢትዮጵያውን ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲና (ኢዜማ)፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አሁን ያለው መንግስት ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረገውን ሽግግር እንዲመራ ሲደግፉ፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንደነት (አብሮንት) ደግሞ “የሽግግር መንግስት” ይቋቋም ብሎ እየሞገተ ይገኛል፡፡
በአንፃሩ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ መጀመሪያም ቢሆን ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጁነት አልነበረውም፤ አሻሚ የሚባል አንቀጽ በህገመንግስቱ እስከሌለ ድረስ የህገመንግስት ትርጉም የሚለው አማራጭ አያስኬድም ብሏል፡፡
የህወሀት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አዲስዓለም ባሌማ “የዚህ አመት ምርጫ አሁን ኮሮና መጣ እንጅ መጀመሪያም ሲልከሰከስ ነበር የመጣው፤ ያው መንግስትም በሙሉ ልብ ምርጫውን አካሂዳለሁ ብሎ ይዞ ሲገፋው ነው የነበረው፣ የቆየ ነገር አልነበረም፡፡ ከመጀመሪያውም ቢሆን ያዝ ለቀቅ ነበር፤መንግስት በዚህ ላይ ጠንካራ አቋም አልነበረውም፡፡”
አቶ አዲስአለም ይሄን ያሉት ባለፈው ሀሙስ በአዲስ አባባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው፡፡
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ“ብልጽግና ምርጫው አይደረግም የሚል እምነትም፣ ፍላጎትም የለውም፤ መንግስት ከመጀመሪያውኑ አቋሙ የተለሳለሰ ነበር የሚለው ተቀባይነት አይኖረውም፡፡”
በቅርቡ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት የ“ህገመንግስት ትርጉም” ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ ያስፈልጋል እያሉ ሲወተውቱ ነበር፡፡
ነገርግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ሕገ መንግስቱ ከሚፈቅደው ውጭ ስልጣን ለመያዝ የሚደረግ እንቅስቃሴን መንግስት እንደማይታገና እርምጃም እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡