የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በማሰብ ለ”ሰብዓዊነት ግጭት የማቆም ውሳኔ” ማሳለፉን አስታውቋል
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም የጥቃት እንቅስቃሴ እንዲታቀቡና በጉልበት ከያዟቸው የአጎራባች ክልሎች ለቀው እንዲወጡ ጠይቋል፡፡
የመንግስት ኩሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ በማሰብ ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታውቋል፡፡
መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች አቅርቦቱ እንዲመቻች እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ እርዳታ የአየር በረራዎች ቁጥር እንዲጨምር እንዲሁም ለእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የነዳጅ እና የጥሬ ገንዘብ የሚቀርብበትን ስርዓት የተሳለጠ እንዲሆን ተደርጓል ብሏል።
የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እርዳታዎችን ማድረስ እንዲችሉ የአየር በረራ መመቻቸቱንም መንግስት ገልጿል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኢትዮጵያ መንግስት በአብአላ- መቀሌ የየብስ ትራንስፖርት መስመር በኩል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መድረስ እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ እያደረኩ ነው ብሏል፡፡
የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፉ እንዲደርስ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ የመንግስት ጥረት እና ቁርጠኝነት የሰብዓዊ ሁኔታውን በማሻሻል ረገድ የሚኖረው ስኬት የሚረጋገጠው በሌላኛው ወገን የሚገኘው አካል በተመሳሳይ ለዚህ አላማ በሚኖረው ቁርጠኝነት ልክ መሆኑን እንደሚያምንም መንግስት ገልጿል።
በመንግስት በኩል የተላለፈው ውሳኔ አላማ የአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ በነጻነት ተጓጉዞ ለእርዳታ ፈላጊ ዜጎች ለመድረስ እንዲችል ነውም ተብሏል።
መንግስት የወሰነው ለሰብዓዊነት ግጭት የማቆም ውሳኔ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዲችል በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም የጥቃት እንቅስቃሴ እንዲታቀቡና በጉልበት ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ ጠይቋል፡፡
በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ህይወት ለመታደግ እና የዜጎችን እንግልት ለመቀነስ ይቻል ዘንድ ከተለመደው የተለዩ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መንግስት ይህ ውሳኔ ከወጣበት ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔውን አስተላልፏል።
ዓለም ዓቀፉ የለጋሾች ማህበረሰብ እያቀረበ ያለውን ድጋፍ እና እርዳታ በከፍተኛ መጠን እንዲጨምርም መንግስት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ይህ ውሳኔ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ በእጅጉ ሊያሻሽል እንደሚችል ብሎም በቀጣይ ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል መንግስት ተስፋ አድርጊያለሁ ብሏል፡፡