ጦርነቱ በሰሜን ወሎ እና ዋግህምራ ዞኖች በተማሪዎች እና መምህራን ላይ ምን ስሜት ፈጠረ?
ተማሪዎች ይህንን ዘመን የማያስታውሱበት ጊዜ እንዲመጣ መሰራት አለበት ተብሏል
ተማሪዎች “የወታደር ደንብ ልብስ እና የወታደር መኪና ባዩ ቁጥር እየተረበሹ”ነው ይላሉ መምህራን
መምህር ንጉስ ተገኑ በቆቦ ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡ መምህሩ በአካባቢያቸው በጦርነቱ ምክንያት በዚህ ዓመት ትምህርት ባለመኖሩ ተማሪዎች እና መምህራን ስሜታቸው መጎዳቱን ይናገራሉ፡፡
የአማራ ክልል ከሰሞኑ ጦርነት በነበረባቸው ዞኖች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀመር መመሪያ ማስተላለፉን ተከትሎ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት መምህር ንጉስ፤ በሰሜን ወሎ በተካሄደው በነበረው ጦርነት ምክንያት ተማሪዎች ስነልቦናቸው መጎዳቱን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ተማሪዎች የወታደር ደንብ ልብስ (ሚሊተሪ ልብስ) እና የወታደር መኪና ባዩ ቁጥር እየተረበሹ ስለመሆኑ ያነሱት መምህሩ፤ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ ሳሉም በጦር መሳሪያ ጩኸት በመሳቀቃቸው በር እንኳን ሲዘጋ በሚፈጥረው ድምፅ ሲበረግጉ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
በቆቦ ከተማ ትምህርት ከተቋረጠ በኋላ በተማሪዎች ላይ ተስፋ መቁረጥ ፣መፍዘዝ፣ የውይይት አቅም መቀነስና ሌሎችም መዳከሞች መታየታቸውን የገለጹት መምህር ንጉስ ተገኑ፤ ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው በደረሰባው ወከባ፤ ፈሪ እና ከቤት የማይወጡ እንዲሁም የሰው ድምፅ በሰሙ ቁጥር የሚደነግጡ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሌላው መምህር ግርማ መክብብ በዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ የሚገኘው ዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ት/ ቤት ርዕሰ መምህር ናቸው፡፡ እርሳቸውም ልክ የቆቦው መምህር ስለተማሪዎች እንደተናገሩት ንጉስ ሁሉ በዚህ ጦርነት ምክንያት ተማሪዎች እየበረገጉ፤ ፍርሃትም እየተሰማቸው መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ነሀሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በህወሃት ቁጥጥር ስር ገብታ የነበረችውና በሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው የቆቦ ከተማ ጉዳት ከደረሰባቸው ከተሞች አንዷ መሆኗን ያነሱት ርዕሠ መምህሩ፤ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁሳዊና ስነልቦናዊ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው ይህ የሆነውም በጦርነቱ ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ነው ብለዋል፡፡
የደረሰው ጉዳት ከግብዓትና ከስነ ልቦና አንጻር ከፍተኛ መሆኑ ተማሪዎች እና መምህራን ጫና ውስጥ እንዲገቡ አድርጓልም ብለዋል፡፡ የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ት/ ቤት ርዕሰ መምህር ግርማ በትምህርት ቤቱ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ የቤተ ሙከራ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች የት/ቤቱን መሰረተ ልማት ላይ ውድመት በመድረሱ የተማሪዎቹን ስነልቦና እንዲጎዳ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
በቆቦ ከተማ የሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ት/ቤት ርዕሰ መምህር ንጉስ ተገኑ እንደሚሉት ት/ ቤቶች እንደአመሰራረታቸው የአካበቱት ሀብት ማለትም ኮፒውተር፣ ፕላዝማ፣ የተማሪ መቀመጫ ወንበር፣ የቤተ ሙከራ ቁሳቁስ፣ የላይብሪ መፃህፍት፣ የመማሪያ መፅሀፍት የተማሪ መረጃዎች እና ሌሎችም ሙሉ በሙሉ በወድደማቸው ተማሪዎችና መምህራንን ትካዜ ውስጥ አስገብቷል ይላሉ፡፡
የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ት/ ቤት ርዕሰ መምህር ግርማም ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ “በዚህ መጡ፤ በአበርገሌ መጡ” ሲባል ስለነበር እየተባለ መደናገጥ ሲፈጠር እንደነበር ጠቅሰው ይህ እንዳይደገም መንግስት ከስር መሰረቱ መስራት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ በመምህራን ላይ የሞራል እና የስነልቦና ጥቃት መድረሱን የሚያነሱት የቆቦው መምህር በግል ት/ቤት መምህራን ላይ ደመወዝ በመቋረጡ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር አጋጥሟቸዋል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ግርማ መክብ ርዕሰ መምህር በመሆን እያገለገሉበት ያለው ትምህርት ቤት ውድመት ቢያፈጋጥመውም ፤ ተማሪዎች ከጦርነት ስነልቦና መውጣት ስላለባቸው ከነጉድለቱም ቢሆን ትምህርት ለመጀመር መታሰቡን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ካለው ድጋፍ ማድረግ አለበት ያሉት ፤ የሰቆጣው መምህር፤የአካባቢው ማህበረሰብ ልጆቹ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ በማድረግ ልጆቹ ይህንን ዘመን የማያስታውሱበት ዘመን እንዲመጣ ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት ከአካባቢያቸው ካልራቀ አሊያም ካልተወገደ ትምህርትና መሰል ስራዎችን መስራት እንደሚያስቸግር በዋግ ኽምራ ዞን ሰቆጣ ከተማ የሚገነው የዋግ ስዩም አድማሱ ወሰን ት/ ቤት ርዕሰ መምህር ግርማ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊማተቤ ታፈረ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በቆዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ4ሺህ የሚበልጡ የትምህርት ተቋማትን ማውደሙን ገልጸው ነበር። ኃላፊው ከአንድ ወር በፊት በባህር ዳር በተካሄደ መድረክ ላይ የወደሙ ትምህርት ቤቶች ገንብቶና ጠግኖ መልሶ የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ከ11 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች በመውደማቸው ከ1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዲሁም 116 ሺህ መምህራን ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ከአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) “አሸባሪው ህወሓት የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ በሚቀረፅባቸው የትምህርት ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል” ማለታቸው ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሰኔ ወር የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ፤ መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ለበርካታ ወራት የቆዩባቸው የሰሜን ወሎና የዋግህምራ ዞኖች ናቸው፡፡ የህወሓት ሃይሎች ለሰላም ሲባል ከአማራ እና አፋር ክልል እንደወጡ ቢያሳውቁም፣ የህወሓት ኃይሎችን በማሸነፍ ይዟቸው ከነበራቸው ቦታዎች ማስቀጣቱን መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡