“በኢትዮጵያ ግጭት ተዋንያን መካከል ያለው ዋና ልዩነት፤ ‘የሰላም መንገዱ ምን ይሁን’ የሚል ነው”- ኦባሳንጆ
የዛሬ ሳምንት ወደ መቀሌ አቅንተው ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የመከሩት ኦባሳንጆ ከኦሮሚያ እና አማራ ክልል ባለስልጣናት ጋር አበረታች ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል
ኦባሳንጆ ወደ ለመወያየት እንዲቻል ሁሉም አካላት ውጊያ ያቁሙ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል
የኢትዮጵያ መንግስት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብር የተፈረጀው ሕወሃት እያደረጉት ያለውን ውጊያ እንዲያሙ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
የኮሚሽነሩ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የመንግስትን እና የህወሃትን አመራሮችን ማነጋገራቸውን ካስታወቁ በኋላ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
“በአዲስ አበባ እና በሰሜን ያሉ ሁሉም መሪዎች ችግራቸው ፖለቲካዊ እንደሆነና ፖለቲካዊ መፍትሄን እንደሚፈልግ በግለሰብ ደረጃ ተስማምተዋል”- ኦባሳንጆ
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሁሉም ወገኖች ወታደራዊ ፍልሚያውን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ከመንግስትም ሆነ ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀው ህወሃት በኩል የሰላም ፍላጎቶች መኖራቸውን የገለጹት ከፍተኛ ተወካዩ ‘የሰላም መንገዱ ምን ይሁን’ የሚለው ግን ልዩነታቸው እንደሆነ ጠቅሰዋል በመግለጫቸው፡፡
ኦባሳንጆ፤ ውጊያው ከቆመ የንግግር ዕድል እንደሚኖር የገለጹ ሲሆን አሁን ባለው ሁኔታ ውጊያ እየተደረገ ግን ለመነጋጋር የሚመች እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት፤ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ኦባሳንጆ ገለጻ ተደረገለት
የአፍሪካ መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ሕብረቱ የጀመረውን የማሸማገል ጥረት እንዲደፉ እና ግጭቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ ነገሮች እንዲቆጠብም ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ጥሪ ያቀረቡም ሲሆን ሆን ተብሎም ይሁን ባለማወቅ ግጭቱን የሚባብሱና ወደከፋ ደረጃ ከሚያደርሱ ንግግሮች መቆጠብ ያስፈልጋል ብለዋል ኦባሳንጆ፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የኦሮሚያ እና አማራ ክልል አመራሮችን ማግኘታቸውን ገልጸው በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የአፋር ክልል አመራሮችን እንደሚያገኙም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ይህ የማሸማገል ስራ እንዲሳካ ቁርጠኛ እንደሆኑ የገለጹት ኦባሳንጆ፤ የኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ሱዳን መሪዎችን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አስማሚ ሁኔታ ይፈጠራል ብዬ አስባለሁ ያሉት ከፍተኛ ተወካዩ፤ ሁለቱም ወገኖች ሰላም፣ ጸጥታና የኢትዮጵያ መረጋጋት ምኞታቸው መሆኑን እንደገለጹላቸው ገልጸዋል፡፡