ሩሲያ በክሬሚያ ጉዳይ የኑክሌር ጥቃት ልትጀምር እንደምትችል ዛተች
ክሪሚያን ከሩሲያ ለመውሰድ ከተሞከረ ማንኛውም አካል በኑክሌር ይቀጣል ስትል አስጠንቅቃለች
ምዕራባዊያን ዩክሬን በክሪሚያ ጥቃት እንድትሰነዝር በማነሳሳት ላይ መሆናቸውን ሩሲያ ገልጻለች
ሩሲያ የኑክሌር ጥቃት ልትጀምር እንደምትችል አስጠነቀቀች።
በቅርቡ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የሩሲያ እና ዩክሬን በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።
ምዕራባውያን ሀገራት በአሜሪካ አስተባባሪነት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለዩክሬን በመለገስ ላይ ሲሆኑ ዩክሬንም የተጠናከረ አዲስ ዘመቻ በሩሲያ ላይ ለመልፈት በዝግጅት ላይ መሆኗን አስታውቃለች።
የሩሲያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት እና የጸጥታ ምክር ቤት ምክትል ሀላፊ ድሚትሪ ሜድቬዴቭ እንዳሉት ዩክሬን በምዕራባዊያን ጉትጎታ በክሪሚያ ላይ ጥቃት እንድትከፍት እየገፋፏት ነው ብለዋል።
- የሩሲያ ፍርድ ቤት ጦርነትን ተቃውሟል ያለውን ወታደር የ6 ዓመት ገደማ እስር ፈረደበት
- የኃያላኑ ሩሲያና ቻይና መሪዎች "አዲስ የዓለም ስርዓት" እንፈጥራለን አሉ
ሜድቬዴቭ አክለውም ዩክሬን ጉትጎታውን ተቀብላ ክሪሚያን ከሩሲያ ለመንጠቅ ጥቃት ብትሰነዝር የኑክሌር ጥቃት ይደርስባታል ብለዋል።
ክሪሚያ በፈረንጆቹ 2014 ላይ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ከዩክሬን ወደ ሩሲያ የተጠቃለለች ቢሆንም ዩክሬን እስካሁን እውቅና አልሰጠችም።
ክሪሚያ የሩሲያ አንድ አካል መደረጓን ተከትሎ በክሪሚያ የሚፈጸሙ ማናቸውም ጥቃቶች በሩሲያ ላይ እንደተፈጸሙ ይቆጠራል ያሉት ሜድቬዴቭ ጥቃት ከተሰነዘረ የሀገሪቱን ሉዓላዊ ግዛት ለመጠበቅ የተዘጋጀው ኑክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል ።
ሩሲያ ያላት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ የሚውለው የሀገሪተ ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ ሲገባ ነው የሚል ህግ እንዳላትም ድሚትሪ ሜድቬዴቭ ጠቅሰዋል ሲል አርቲ ዘግቧል።
ሜድቬዴቭ አክለውም ዩክሬን በምዕራባዊያን ሀገራት ጫና እየተደረገባት ቢሆንም በክሪሚያ ጥቃት ለማድረስ እንደማትሞክር ተናግረዋል።
ዩክሬን ከምዕራባዊያን ሀገራት ቃል የተገባላት የአየር እና ምድር ላይ የጦር መሳሪያ ድጋፎችን በማሰባሰብ ላይ ስትሆን አሁን ያለው ቀዝቃዛ ወራት ሲገባደድ አዲስ ጥቃት ለማድረስ በዝግጅት ላይ መሆኗም ተገልጿል።
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የሚለገሱት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የጦርነቱን ጊዜያት ከማራዘም በዘለለ የሚፈጥሩት ነገር የለም ብላለች።