ኤለን መስክና ማርክ ዙከርበርግ ከቃላት መወራወር ይልቅ በቡጢ ፍልሚያ ይዋጣልን ብለው ሳይገናኙ መቅረታቸው ይታወሳል
የሜታ ንብረት የሆነው ዋትስአፕ የመልዕክት ልውውጥ ስርአቱ ደህንነቱ የተጠበቀ አለመሆኑን አሜሪካዊው ቢሊየነር ኤለን መስክ ተናገሩ።
የኤክስ (ትዊተር) ባለቤቱ መስክ በዋትስአፕ ላይ ትችት ሲሰነዝሩ የሰሞኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
አንድ የኤክስ ተጠቃሚ "የዋትስአፕ መልዕክቶች ከላኪው ወደ ተቀባዩ ያለምንም ጣልቃገብነት የሚደርስ ከሆነ ለእኔ የቀረቡ የሚመስሉ ማስታወቂያዎችን እንዴት ልመለከት ቻልኩ?" የሚል ፅሁፍ ይለጥፋል።
መስክም በዚህ ፅሁፍ ስር አጭር መልስ ሰጥቷል፤ "ምክንያቱም ዋትስአፕ ሰላይ ስለሆነ ነው" የሚል።
የቴክኖሎጂ ቢሊየነሩ ኤለን መስክ በተቀናቃኙ ማርክ ዙከርበርግ መተግበሪያዎች ላይ ተደጋጋሚ ወቀሳ በማሰማት ይታወቃሉ።
ባለፈው ግንቦት ወርም "ዋትስአፕ የእያንዳንዱን ተጠቃሚ መረጃ ማታ ማታ በማውረድ ይተነትናል፤ ይህ መረጃም ለታለመ የማስታወቂያ ስራ ይውላል፤ ለዋትስአፕ ተጠቃሚዎቹ ምርት እንጂ ደንበኛ አይደሉም" የሚል አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል።
" አንዳንድ ሰዎች አሁንም ዋትስአፕ ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ብለው ያምናሉ" የሚሉት የቴስላና ስፔስኤክስ ስራ አስፈፃሚው መስክ፥ ዋትስአፕ እንደ ፌስቡክ ካሉ የሜታ ኩባንያዎች ጋር መረጃ እንደሚለዋወጥ ይገልፃሉ።
የዋትስአፕ ሃላፊው ዊል ካትካርት ግን የመስክን ተደጋጋሚ ትችት መሰረተ ቢስ ነው በሚል ማጣጣላቸውን አርቲ አስነብቧል።
"ለደንበኞቻችን የመረጃ ደህንነት ቅድሚያ ስለምንሰጥ ነው ከላኪ ወደ ተቀባይ ሙሉ በሙሉ ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲደርስ የምናደርገው" ያሉት ካትካርት፥ የመስክን ክስ ውሃ የማያነሳ ነው ብለውታል።
የሳይበር ደህንነት ተመራማሪው ቶሚ ማይስክ በበኩላቸው ምንም እንኳን የዋትስአፕ የመልዕክት መላኪያ ስርአት ደህንነቱ የተጠበቀ (ኢንክሪፕትድ) ነው ቢባልም የተጠቃሚዎች መረጃ መልዕክቱ ብቻ አይደለም ባይ ናቸው።
ሜታ የተጠቃሚዎች መኖሪያ አድራሻ፣ በተደጋጋሚ የሚያወሯቸው ሰዎች ማንነትና መተግበሪያውን በብዛት የሚጠቀምበት ጊዜን የተመለከቱ መረጃዎችን ለውጤታማ የማስታወቂያ ስርጭት እንደሚጠቀምበት በማውሳትም ዋትስአፕም ከዚህ ውጭ ሊሆን አይችልም ብለዋል።
ኤለን መስክ በ2022 ትዊተርን (ኤክስ) ለመግዛት ጥረት ማድረግ ከፈሲጀምሩ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራምና ዋትስአፕን የጠቀለለውን ሜታ ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ የቴክኖሎጂ "አምባገነን" በማለት መተቸታቸው አይዘነጋም።
ሁለቱ ቢሊየነሮች በተለይ ሜታ ባለፈው አመት ትሪድስ የተሰኘና ከትዊተር ጋር የተቀራረበ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ከከፈተ በኋላ የቃላት መወራወራቸው በርትቶ ነበር።
መስክ እና ዙከርበርግ በቡጢ ፍልሚያ ይዋጣልን ብለው ልምምድ መጀመራቸው ትኩረት ቢስብም ተጠባቂው ግጥሚያ ሳይካሄድ ቀርቷል።