የዘንድሮው ረመዳን ጾም መቼ ይጀመራል?
ጾሙ ከመጀመሩ በፊት አማኞች ምን ምን ማድረግ አለባቸው?
የረመዳን ጾም ከአምስቱ የእስልምና ማዕዘናት መካከል አንዱ ነው ተብሏል
የዘንድሮው ረመዳን ጾም መቼ ይጀመራል?
በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የረመዳን ጾም ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
አል አረቢያ እንደዘገበው ከሆነ የዘንድሮው የረመዳን ጾም የካቲት 21 ቀን አልያም በማግስቱ ይጀመራል የተባለ ሲሆን ለአንድ ወር ይቆያል ተብሏል፡፡
ጤነኛ የሆኑ የእስልምና አማኞች በሙሉ ይጾሙታል የሚባለው ይህ የረመዳን ወር የእስልምና ዕምነት ካሉት አምስት ማዕዘናት መካከል አንዱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
አማኞችን ከፈጣሪያቸው ጋር የበለጠ ያቀራርባል በሚባለው በዚህ ጾም ወቅት ሀገራት ለዜጎቻቸው የስራ ጫና እንዳይበዛባቸው የሚያደርጉበትም ነው፡፡
የዕምነቱ ተከታዮች ይህ የጾም ወቅት ከመድረሱ በፊታ ራሳቸውን በተለያዩ መልኮች እያዘጋጁ ሊቆዩ ይገባል የተባለ ሲሆን ለአብነትም ሰውነትን ጾም ማለማመድ አንዱ ነው፡፡
እንዲሁም ጾሙ ከመድረሱ በፊት የምግብ መጠንን ለመቀነስ መሞከር፣ አስቀድሞ የበጎ ፈቃድ ጾሞችን መጀመር እና መደበኛ የመመገቢያ ሰዓት ላይ ማሻሻያ ማድረግም ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
በተለይም እንደ ቡና እና መሰል አነቃቂ መጠጦችን አብዝተው የሚጠቀሙ ሰዎች በጾሙ ወቅት ላለመቸገር አስቀድመው ቢያቆሙ አልያም ቢቀንሱ የተሻለ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ጾሙ ከመግባቱ በፊት አስቀድመው የሚያጨሱትን ሲጋራ መጠን ቀስ በቀስ መቀነስ ሌላኛው ከጾሙ በፊት መሰራት ያለበት ቅድመ ዝግጅት ነውም ተብሏል፡፡
ምግብ አርፍደው መመገብ የለመዱ ሰዎች ቁርሳቸውን ቀደም ብለው መመገብን መለማመድ፣ የሚመገቧቸውን አማራጭ ምግቦችን መቀነስ እና መሰል ዝግጅቶችን አስቀድመው መደረግ እንዳለባቸውም ተጠቅሷል፡፡