በዘንድሮው ምርጫ ከሚጠበቀው ከፍተኛ ፉክክር የተነሳ የአሸናፊው ማንነት ቶሎ ላይገለጽ እንደሚችል እየተነገረ ነው
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዋና ዋና ሁነቶች
በሚሊየን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ቀጣዮቹን አራት አመታት ሀገሪቱን የሚያስተዳድረውን አዲሱን ፕሬዝዳንታቸውን በዛሬው እለት ይመርጣሉ፡፡
የአሜሪካ ምርጫ ውጤት አንዳንድ ጊዜ የምርጫ ጣብያዎች በተዘጉ በሰዓታት ውስጥ ይታወጃል፡፡
- ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም የሚሞክሩ ከሆነ ሊገደሉ እንደሚችል የቀድሞው የሩሲያ ፕሬዝዳንት ተናገሩ
- ትራምፕ አልያም ሃሪስን ለድል የሚያበቁ 10 ምክንያቶች
ነገር ግን የዘንድሮው ምርጫ ጥብቅ ፉክክር የሚደረግበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውጤቱን ለማወቅ ረዘም ያለ ጊዜን ሊወስድ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
ከምርጫ ቀን አንስቶ እስከ ውጤት ገለጻ እና በዓለ ሲመት ድረስ የአሜሪካ ምርጫ ዋና ዋና ሁነቶች ምንድን ናቸው፡፡
የ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት የሚገለጸው መቼ ነው?
በአሜሪካ ከሚገኘው የተለያየ የሰአት አቆጣጠር (ታይም ዞን) ጋር በተገናኝ የመጀመርያው የምርጫ ጣብያ ማክሰኞ ምሽት 12 ሰአት ላይ የሚዘጋ ሲሆን የመጨረሻው ደግሞ እሮብ ንጋት ላይ ይዘጋል፡፡
በአንዳንድ የምርጫ ውድድሮች ምርጫው በተካሄደበት ቀን ምሽት ላይ አልያም በቀጣዩ ቀን ጠዋት አሸናፊው ይታወጃል፡፡
እንደዘንድሮው አይነት ብርቱ ፉክክር እየተካሄደበት እንደሚገኘው ምርጫ ሲያጋጥም ጠባብ ውጤቶች የምርጫ ውጤትን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዳይከቱ ድምጾች ድጋሚ ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡
የምርጫ ውጤቱን ይወስናሉ በሚባሉ ግዛቶች በአሸናፊው እና በተሸናፊው መካከል የ50 በመቶ ድምጽ ልዩነት ካለ ድጋሚ ይቆጠራል፡፡
ከዚህ ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች ውጤቱ በምን ያህል ፍጥነት ይፋ ሆነ?
በ2020 በተደረገው ምርጫ ጆ ባይደን በፔንሴልቫኒያ የነበረው ድምጽ ተቆጥሮ እስከሚያልቅ ድረስ ለአራት ቀናት አሸናፊ መሆናቸው አልተረጋገጠም ነበር፡፡
በአንጻሩ በ2016 ዶናልድ ትራምፕ የምርጫ ጣብያዎች በተዘጉ በሰአታት ልዩነት ውስጥ አሸናፊነታቸው ታውጇል፡፡
በ2012 ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ የስልጣን ዘመን በተወዳደሩበት ምርጫ አሸናፊነታቸው የተገለጸው ምርጫ በተደረገበት ቀን እኩለ ሌሊት ላይ ነበር፡፡
በአንጻሩ በጆርጅ ቡሽ እና በአል ጎር መካከል በ2000 በተደረገው ምርጫ ውጤት ለማወቅ አሜሪካውያን አምስት ሳምንታትን ጠብቀዋል፡፡
የምርጫ ውጤቱ የሚቆጠርበት መንገድ
በቅድሚያ ምርጫው በተደረገበት ቀን የተሰበሰቡ ድምጾች ተቆጥረው ካለቁ በኋላ ከምርጫው ቀደም ብሎ በፖስታ እና በተለያዩ መንገዶች የተሰጡ ድምጾች ፣ ከሀገር ውጭ ካሉ ዜጎች እና ወታደሮች የተሰበሰቡ ድምጾች ይታከልበታል፡፡
የአካባቢ ምርጫ አስፈጻሚዎች አንዳንድ ጊዜ በሹመት ሌላ ጊዜ ደግሞ ተመርጠው ምርጫውን ያስፈጽማሉ፤ የግለሰቦችን ድምጽ ይቆጥራሉ፤ እንዲሁም አጠቃላይ ሂደቱን የማሳለጥ ሃላፊነትን ይወጣሉ፡፡
በዋናት ቆጠራው የሚካሄደው እያንዳንዱን የምርጫ ወረቀት ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ መቁጠርያ ሳጥን ውስጥ በማስገባት የእጩዎቹን ውጤት በሰንጠረዡ ውስጥ ያካትታል፡፡
በአንዳንድ ሁኔታዎች በእጅ ቆጠራ ወይም ድጋሚ ማረጋጋጫ ሊደረግበት ይችላል፡፡
ተወዳዳሪዎች በምርጫው እኩል ድምጽ ቢያገኙ ምን ይደረጋል?
ሁለቱም ዕጩዎች እኩል 269 የወኪል መራጮች ድምጽ ስላላቸው አንዳንድ ጊዜ እኩል ውጤት የሚመዘገብበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡
በዚህ ሁኔታ የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአሜሪካ ኮንግረስ (የታችኛው ምክር ቤት) አስቸኳይ ምርጫ በማድረግ ፕሬዝዳንቱን ይሰይማሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሴኔቱ በበኩሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ምርጫ ያከናውናል፤ ነገር ግን እጩዎች በምርጫው እኩል ድምጽ የማግኝት አጋጣሚ ለ200 አመታት ተከስቶ አያውቅም፡፡
የአዲሱ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት መች ይከናወናል?
ተመራጩ 47ተኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዕለተ ሰኞ ጥር 20፣ 2025 በዓለ ሲመቱን ካከናወነ በኋላ የስልጣን ዘመኑን አንድ ብሎ ይጀምራል፡፡
የዘንድሮው በዓለ ሲመትም በአሜሪካ ታሪክ ለ60ኛ ጊዜ የሚደረግ ሆኖ በታሪክ ይመዘገባል፡፡
ከስልጣን ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ቤተሰቦቹ ፣ የፓርቲ አባላት ፣ ደጋፊዎች እና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት አዲሱ ፕሬዝዳንት ህገ መንግስቱ ላይ እጁን በማስደገፍ ቃለ መሀላ ከገባ በኋላ የመጀመርያ ይፋዊ ፕሬዝዳንታዊ ንግግሩን ያደርጋል፡፡