ገናን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያከብሩት ሀገራት እነማን ናቸው?
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ሀገራት ክርስቲያኖች የገና በዓልን ከ12 ቀናት በፊት ማክበራቸው ይታወሳል
ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽ፣ ሩስያ እና ዩክሬንን ጨምሮ 14 ሀገራት የገና በዓልን በዛሬው እለት እያከበሩ ነው
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና) በምስራቅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ በዛሬው እለት እየተከበረ ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የጁሊያን የዘመን ቀመር የሚከተሉት ሀገራት ናቸው በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ስነ ስርአቶች በዓሉን እያከበሩ የሚገኙት።
ከአለማችን ህዝብ 12 ከመቶው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኑን ታይም መጽሄት ይዞት በወጣው መረጃ ያመላክታል።
በምስራቅ አውሮፓ፣ መከከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ኢትዮጵያ እና ግብጽ ከፍተኛ የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር ይገኝባቸዋል።
የዘመን ቀመሯን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ያዋደደችው ኢትዮጵያ 2017ኛውን የልደት በዓል እያከበረች ነው።
በዓሉ በተለይም በላሊበላ የወትሮ ድምቀቱን ይዞ ተከብሯል።
ከ15 ሚሊየን በላይ የግብጽ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ አማኞችም የገና በዓልን በዛሬው እለት እያከበሩት ነው።
በሩሲያም የገና በዓል ዋዜማን በጾም የሚያሳልፉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በዛሬው እለት የገና በዓልን በማክበር ላይ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም እንደወትሯቸው ህዝብ በተሰበሰበበት ባይሆንም በክሬምሊን በሚገኝ ካቴድራል የቅዳሴ ስርአት ላይ መገኘታቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አስነብበዋል።
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት በሚገኙባቸው ኤርትራ፣ እስራኤል፣ አርመኒያ፣ ሰርቢያ፣ ቤላሩስ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ቡልጋሪያ፣ መቄዶኒያ፣ ጆርጂያ እና ሞልዶቫም የገና በዓል በዛሬው እለት እየተከበረ ነው።
የጎርጎሮሳውያኑን የዘመን ቀመር የሚከተሉ ክርስቲያኖች ከአንድ ሳምንት በፊት የገና በዓልን ማክበራቸው ይታወሳል።