ኢራቅ እና ሱዳን በኦሎምፒክ አንድ ሜዳልያ ብቻ በማግኝት በውድድሩ ዝቀተኛ አፈጻጸም ካላቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ
በኦሎምፒክ ውድድሮች በርካታ ሜዳልያዎች ያገኙ ሀገራት የትኞቹ ናቸው?
ኦሎምፒክ በፈረንጆቹ 1896 በግሪክ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተሳታፊዎቹን እና የውድድሮቹን አይነት እያሰፋ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
የዘንድሮው ውድድር በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን በ32 አይነት የስፖርት ውድድሮች ለ329 የወርቅ ሜዳሊያዎች ሀገራት ይፋለማሉ፡፡
የበርካታ ሜዳልያ ባለቤቶችን ደረጃ ለማውጣት የአለም ቅርጽ መቀያየር የኦሎምፒክ ታሪክ አጥኚዎችን ስራ እንደፈተነው ይነገራል፡፡
ለአብነት ወደ 15 ሀገርነት የተቀየረችው የቀድሞዋ ሶቭየት ህበረት ከመበታተኗ በፊት የነበሩ ሜዳልያዎችን ለየትኛው ሀገር እንደሚሰጥ አስቸጋሪ በመሆኑ በሶቭየት ህብረት ስር ተቀምጦ ሩሲያ እንደ ሀገር ከተመሰረተች በኋላ ያስመዘገበችው ደረጃ ለብቻዋ ተመዝግቦላታል፡፡
የክረምት እና በጋ ኦሎምፒክ ተብሎ በተከፈለው አለም አቀፋዊ ውድድር አሜሪካ 3105 ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ በአለም ቀዳሚዋ ስትሆን በተሳተፈችባቸው ውድድሮች 1229 የወርቅ ፣ 1000 የብር እና 876 የነሀስ ሜዳልያዎችን ማግኝት ችላለች፡፡
ጀርመን በ1211 ሜዳልያዎች ስትከተል ፈረንሳይ እና ብሪታንያ በመቀጠል በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በርካታ ሜዳልያ በመስብሰብ ስማቸው የተዘረዘሩ ሀገራት እንዳሉ ሁሉ እንደ ኢራቅ እና ሱዳን ያሉ ሀገራት በውድድሩ አንድ ብቻ ሜዳልያ በማስመዝገብ ይጠቀሳሉ፡፡
በኦሎምፒክ ታሪክ አጥኚዎች እና መዝጋቢዎች እንደሚተዳደር በሚነገረው ኦሎምፒዲያ ኦርግ በወጣው መረጃ መሰረት ታንዛኒያ ፣ ሞዛምቢክ ፣ ኒጄር እና አፍጋኒስታን በኦሎምፒክ ውድድሮች በነበራቸው ተሳትፎ ከሁለት የዘለለ ሜዳልያ ማሳካት ያልቻሉ ሀገራት ናቸው፡፡