የዓለም የጤና ድርጅት ለሰብዓዊ አቅርቦት በአስቸኳይ የጋዛ መንገድ ይከፈትልኝ አለ
ተመድ በፍልስጤም የረዥም ጊዜ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚደርስ አስጠነቀቀ
የዓለም የጤና ድርጅት ጋዛን ለመክፈት ከባለስልጣናቱ ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሏል
የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ ሰብዓዊ እርዳታ እና የህክምና አቅርቦቶችን ለማድረስ አስቸኳይ መዳረሻ ያስፈልገኛል ብሏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በፍልስጤም ግዛት ውስጥ የረዥም ጊዜ ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚደርስ እስጠንቅቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በተቻለ ፍጥነት ጋዛን ለመክፈት ከውሳኔ ሰጪዎች ጋር እየተነጋገረ ነው ብሏል።
ከግብጽ ጋር በሚዋሰነው በራፋ ድንበር በስተደቡብ እርዳታ እያደረሰ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን፤ ወደ ጋዛ ለመግባት የመስመሩን መከፈት እየጠበቀ መሆኑን ገልጿል።
የዓለም ጤና ድርጅት አቅርቦቶቹ ለሦስት ቀናት ዝግጁ ሆነው መቆየታቸውንም ተናግሯል። ሆኖም ሰራተኞቹ እርዳታውን ሊያደርሱ አልቻሉም ብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት የዌስት ባንክ እና የጋዛ ተወካይ የሆኑት ዶክተር ሪቻርድ ፔፐርኮርን የጋዛ ሁኔታ የረጅም ጊዜ ሰብዓዊ ቀውስ ይሆናል ብለዋል።
በጋዛ የእስራኤል የአየር ጥቃት ከጀመረ በኋላ ሁለት ሽህ 800 ሰዎች ሲሞቱ፤ 11 ሽህ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
ቴላቪቭ ባለፈው ሳምንት በደቡባዊ የእስራኤል ከተሞች በደረሰ ጥቃት አንድ ሽህ 300 ሰዎችን የገደሉባትን የሀማስ ታጣቂዎች መደምሰስ ላለመ የምድር ጥቃት እየተዘጋጀች ነው።