የፖላንድ እግር ኳስ ማህበር “ትክክለኛ ውሳኔ ነው”ብሎታል
ፖላንድ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሩሲያ ጋር ያለባትን የእግር ኳስ ጨዋታ ማድረግ እንደማትፈልግ አስታወቀች፡፡
ሁለቱ ሀገራት በፈረንጆቹ መጋቢት 24 ቀን 2022 በሩሲያ እንደሚጫወቱ መርሃ ግብር ቢወጣም፤ ፖላንድ ግን አሁን ባለው የዩክሬን ጦርነት ምክንያት መጫወት እንደማትፈልግ ይፋ አድርጋለች፡፡ በተመሳሳይ ዕለት አሁን ጦርነት ላይ ያለችው ዩክሬን ከስኮትላንድ ጋር ትጫወታለች የሚል መርሃ ግብርም ወጥቶ ነበር፡፡
ፖላንዳዊው የባየርሙኒክ አጥቂ ሮበርት ሎዋንዶስኪ ሀገሩ ከሩሲያ ጋር ላለመጫወት መወሰኗ “ትክክለኛ” ውሳኔ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የ 33 ዓመቱ አጥቂ ሎዋንዶስኪ፤ የፖላንድ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አግቢ ሲሆን “በዩክሬን የወረራ ጦርነት ባለበት ሁኔታ ከሩሲያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመጫወት ጭራሽ አላስብም” ማለቱም ተሰምታል፡፡ ለዚህ ሁኔታ “የሩሲያ እግር ኳስ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ተጠያቂ ናቸው” ብሎ እንደማያምን የገለጸው ተጫዋቹ “ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገን ማስመሰል የለብንም” ብሏል፡፡
ስዊድን እና ቼክ ሪፐብሊክም በማጣሪያው ከተጫወቱ በኋላ አሸናፊው ከሩሲያ ጋር እንደሚጫወት ይጠበቃል፡ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ፖላንድ፣ ስዊድን እና ቼክ ሪፐብሊክ በሩሲያ አንጫወትም ካሉ በኋላ ሁኔታውን በደንብ እንደሚከታተለው ገልጿል፡፡
የፖላንድ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሴዛሪ ኩሌዛ ከሩሲያ ጋር ለመጫወት ምንም አላማ እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡ አሁን ጊዜው ውሳኔ የሚወሰንበት ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የፖላንድ እግር ኳስ ማህበር ከስዊድን እና ቼክ ሪፐብሊክ ጋር በመነጋገር ለፊፋ ተመሳሳይ አቋማቸውን እንደሚቂርቡም ተገልጿል፡፡