ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን በድጋሚ ተመረጡ
በጄኔቫ እየተካሄደ ያለው 75ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ የዶ/ር ቴድሮስ በድጋሚ መመረጥ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ አድርጓል
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለም ጤና ድርጅት ለመምራት በድርጅቱ ቦርድ የቀረቡ የተወዳደሩ ብቸኛ እጩ ነበሩ
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር በመሆን በድጋሚ ተመረጡ።
በጄኔቫ የተሰባሰቡት የዓለም ጤና ድርጅት አባል ሀገራት ተወካዮች ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለሚቀጥሉት አምስት አመታት የድርጀቱ ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲያገለግሉ በድጋሚ መርጧዋል።
በጄኔቫ እየተካሄደ ያለው 75ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ የዶክተር ቴድሮስ በድጋሚ መመረጥ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ አድርጓል።
የዓለም ጤና ድርጅት ቦርድ ቀደም ሲል ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖምን ለድርጅቱ ዋና ዳይሬክተርነት ብቸኛ እጩ አድርጎ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
በዚህም ጀርመንን የመሳሰሉ ሀገራት ለዋና ዳይሬክተሩ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ከአሁን ቀደም ማሳወቃቸው አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ ዶክተር ቴድሮስ ብቸኛ እጩ ሆነው በቀረቡበት ወቅት፤ ግለሰቡ ከተጣለባቸው ሃላፊነት ውጪ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ህወሓት ያደላ የፖለቲካ ውግንና አሳይተዋል የሚል ክስ እና የ‘ይመርመርልኝ’ ጥያቄ ለቦርዱ አቅርባ ነበር።
ሆኖም ቦርዱ በመንግስት የቀረበውን ይህን ጥያቄ አሁን ሊመለከት እንደማይችል በማሳወቅ ዶ/ር ቴድሮስን በድጋሚ እጩ አድርጎ ሊያቀርብ ችሏል።
የቦርዱ ሊቀ መንበር ፓትሪክ አሞጽ “ችግሩ ውስብስብና ፖለቲካዊ መልክ ያለው እና ከኮሚቴው የአሰራር ሂደት ውጭ የሆነም ጉዳይ ነው” ማለታቸውም አይዘነጋም።