ወደ ፍጥጫ የገቡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርና "የትግራይ ሰራዊት" ባወጡት መግለጫ ምን አሉ?
"የትግራይ ሰራዊት" አመራሮች ባወጡት መግለጫ በዶ/ር ደብረጺዮን ለሚመራው የህወሓት ቡድን ድጋፋቸውን ሰጥተዋል
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሰራዊቱ አመራሮች "መፈንቅለ መንግሥት አውጀውብኛል" ብሏል
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና እና "የትግራይ ሰራዊት" በትናንትናው እለት ባወጡት መግለጫ እርስ በራሳቸው ተካሰዋል።
"የትግራይ ሰራዊት" አመራሮች በሰጡት መግለጫ "ጊዜያዊ አስተዳደሩ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የተሰጠው ተልዕኮ ውጪ ክህደት በመፈጸም ለውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን እየሰራ ይገኛል" ብለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በለውጥ ስም የከተማና ወረዳ ምክር ቤቶችን የማፍረስ ተግባር ሊያቆም እንደሚገባና መሰል እንቅስቃሴዎች "በትዕግስት የማይታለፉ ቀይ መስመሮች" መሆናቸውን አመራሮቹ አሳስበዋል።
- “ስልጣን የኔ ነው የሚሉ አካላት ፍላጎታቸውን በኃይል ለማስፈጸም እየጣሩ ነው”- አቶ ጌታቸው ረዳ
- በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት “አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት አንስቻለሁ” አለ
"የትግራይ ሰራዊት" አመራሮች አክለውም፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ተተኪ አመራሮች ሊካተቱበት እንደሚገባ ያስተወቁ ሲሆን፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ተሰፍረው የተሰጡትን ተግባራት ሳይፈጽም የቆይታ ጊዜውን ጨርሷል ብለዋል።
አመራሮቹ 14ኛ ጉባኤውን ያደረገው ህወሓት ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማስተካከል የወሰነው ውሳኔ "ሳይውል ሳያድር ተግባራዊ እንዲደረግ" የትግራይ ሰራዊይ ድጋፍ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ መልስ የሰጠ ሲሆን፤ "የትግራይ ሰራዊት" የበላይ አመራሮች ያወጡትን መግለጫ እንደማይቀበለው አስታውቋል።
በሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ስም በወጣው መግለጫ "መፈንቅለ መንግሥት ታውጆብኛል" ያለው ጊዜዊ አስተዳደሩ፤ "ህጋዊ ላልሆነው ቡድን የወገነ ነው" ሲልም መግለጫው አጣጥሎታል።
የሰራዊቱ አመራሮች መግለጫ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ማፍረስ፣ ስርዓት አልበኝነትን ማንገስና ሰራዊቱን የመበተን ግልጽ ዓላማ ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ያሳየ ነው ሲልም ከሷል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ መጥራቱንም ያሳወቀ ሲሆን፤ የስብሰባው ዋነኛ ዓላማም "ተቀባይነት የሌለው" ውሳኔ ለማረም እንዲቻል ያለመ መሆኑን አስታውቋል።
ከስብሰባው በኋላ ስለጉዳዩ ለህዝቡ በዝርዝር ማብራሪያ እንደሚሰጥም አስተዳደሩ በመግለጫው አስታውቋል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ በሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳር እና በዶ/ር ደብረጺዮን መካከል ካሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የተፈጠረው አለመግባባት እየተባባሰ ይገኛል።
በእነ ደብረፅዮን ገበረ ሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ “አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት አንስቻለሁ” ማለቱም ይታወሳል።
ፓርቲው አቶ ጌታቸውን እንዴትና በማን እንደሚተኩ ከፌዴራል መንግሥትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ይወሰናል ሲል መግለጹም አይዘነጋም።
“ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው በሚመሩት የህወሓት ቡድን የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ይፋዊ መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሷል።
የሁለቱ ቡድኖች አለመግባባት ወደ ግጭት እንዳይገባ የትግራይ የጸጥታ ኃይል እጁን እንዳያስገባ ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል።