የጋዛው አልሽፋ ሆስፒታል 'የሞት ቀጣና" ሆኗል- የአለም ጤና ድርድት
በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት እስካሁን ከ11ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል
በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ውስጥ 25 የጤና ባለሙያዎች እና 32 ህጻናትን ጨምሮ 291 ታካሚዎች እንደሚገኙ ተገልጿል
የአለም ጤና ድርጅት የጋዛውን አል ሽፋ ሆስፒታል "የሞት ቀጣና" ሲል ገልጾታል።
የሰብአዊ እርዳታ ገምጋሚ ቡድን በሰሜን ጋዛ የሚገኘውን የአልሽፋ ሆስፒታል መጎብኘቱን እና ሁኔታው "የሞት ቀጣና" እንደሆነ የሚያሳይ ነው ማለቱን ድርጅቱ በትናንትናው እለት ገልጿል።
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ የፐብሊክ ሄልዝ ባለሙያዎችን፣ የሎጂስቲክ ኃላፊዎችን እና ከተለያዩ የተመድ ክፍሎች የጸጥታ አካላትን ያካተተው በድኑ በሆስፒታሉ ውስጥ ለአንድ ሰአት ያህል ቆይታ አድርጓል።
ሆስፒታሉን "የሞት ቀጣና" ብሎ የገለጸው ይህ ቡድን አሁን ላይ ሆስፒታሉ ስራ አቁሟል ብሏል።
"ተኩስ መደረጉን የሚያሳዩ ምልክቶች በደንብ ይታዩ ነበር። በድኑ በሆስፒታሉ መገቢያ ላይ የጅምላ መቃብር ማየቱን እና 80 ሰዎች እንደተቀበሩበት መረዳቱን" ድርጅቱ ገልጿል።
ድርጅቱ የሆስፒታሉ መተላለፊያዎች በቆሻሻ በመሞላቱ የጤና ባለሙያዎች እና ታካሚዎች ለጤናቸው ይሰጋሉ ብሏል።
በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ውስጥ 25 የጤና ባለሙያዎች እና 32 ህጻናትን ጨምሮ 291 ታካሚዎች እንደሚገኙ ተገልጿል።
እስራኤል ሀማስ ሆስፒታሉን የጦር ማዘዣ ጣቢያ አድርጎታል የሚል ክስ አቅርባለች። ነገርግን ሀማስ ክሱ እስራኤል ጥቃቷን ምክንያታዊ ለማድረግ የምትጠቀመዎ "የሀስት ትርክት" ነው ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።
በዛሬ እለት ሀማስ፣ እስራኤል እና አሜሪካ ከአምስት ሳምንት በላይ ያስቆጠረውን ግጭት ለአምስት ቀናት ጋብ ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጿል።
በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት እስካሁን ከ11ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።